ሀይደር ሸረፋ ወደ መቐለ ከተማ አምርቷል

በዝውውር መስኮቱ ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረጉ ከሚገኙ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው መቐለ ከተማ ሀይደር ሸረፋን በይፋ ማስፈረሙ ታውቋል። 

የቀድሞው የደደቢት እና ሀዲያ ሆሳዕና አማካይ በ2009 ወደ ጅማ አባ ቡና ካመራ በኋላ መልካም ጊዜ ማሳለፍ የቻለ ሲሆን ከክለቡ ጋር ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ ከጫፍ ደርሶ በትላንትናው እለት በሽረ እንዳሥላሴ ተሸንፈው ሳይሳካ ቀርቷል። ሀይደር ከክለቡ ጋር የተስማማው ቀደም ብሎ የነበረ ቢሆንም ጅማ አባ ቡና ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ ወሳኝ ጨዋታዎች የሚጠብቁት በመሆኑ ይፋ ሳይደረግ ቆይቶ በመጨረሻም ለመቐለ ለአንድ ዓመት ለመጫወት የተስማማ ሲሆን በጅማ አባ ቡና አብሯቸው ከሰራው አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ጋር በድጋሚ የሚገናኝ ይሆናል። 

በተያያዘ ዜና መቐለ ከተማ ኦሲይ ማውሊ ለተባለ ጋናዊ ተጫዋች እና ለቀድሞው የወልዲያ እና መከላከያ ተጫዋች ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ የሙከራ እድል ሰጥቷል።