ኢትዮ ኤሌክትሪክ አሰልጣኞቹን በይፋ አስፈርሟል

ከሦስት ቀናት በፊት በሁሉም ዕርከን ለሚገኙ ቡድኖቹ አዳዲስ አሰልጣኞችን የመረጠው ኤሌክትሪክ ዛሬ ረፋድ ላይ የፊርማ ሥነ ስርዓት አከናውኗል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ9፡00 ጀምሮ ሜክሲኮ በሚገኘው ክበቡ ባደረገው ሥነ ስርዓት ከ15 ዓመት በታች ቡድኑ ጀምሮ እስከ ዋናዎቹ ቡድኖቹ ድረስ ለመረጣቸው አሰልጣኞቹ በይፋ ኃላፊነቱን አስረክቧል። በክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ለገሰ መሪነት የጀመረው ፕሮግራሙ በቀድሞው እና በአሁኑ ቦርድ ውስጥ በአባልነት እያገለገሉ በሚገኙት አቶ መንገሻ ደሴ ንግግር ተከፍቷል። አቶ መንገሻ በንግግራቸው የክለቡን አንጋፋነት አንስተው አሁን የገጠመውን የውጤት መጥፋት እና መውረድ በማስረዳት አዲሱ ቦርድ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በክለቡ ለውጦችን ለማምጣት የመጀመሪያ እርምጃ የሆነው የአሰልጣኞች ቅጥር በይፋ እንደሚፈፀም አብራርተዋል።

በመቀጠል የቦርድ ሰብሳቢ በሆኑት አቶ ኢሳይያስ ደንድር መሪነት በሁሉም ቡድኖች ውስጥ በዋና አሰልጣኝነት የተሾሙት ግለሰቦች ፊርማቸውን ያኖሩበት ሥነ ስርዓት ተካሂዷል። በዚህም መሰረት አሰልጣኝ ናርዶስ በቀለ ከ15 ዓመት በታች ቡድኑን፣ አሰልጣኝ ዳንኤል የሻው ከ17 ዓመት በታች ቡድኑን፣ አሰልጣኝ ኃይሉ አድማሱ ከ20 ዓመት በታች ቡድኑን፣ አሰልጣኝ አንዋር ያሲን ዋናውን የወንዶች ቡድን እንዲሁም አሰልጣኝ እየሩሳሌም ነጋሽ የሴቶች ቡድኑን ተረክበው ለማሰልጠን ከክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ለገሰ ጋር በይፋ ተፈራርመዋል።

አቶ ኢሳይያስ በቀጣይነት ፕሮግራሙ የፊርማ ሥነ ስርዓት ብቻም ሳይሆን ኃላፊነትን የመስጠት እንደሆነ ገልፀው ተሿሚ አሰልጣኞች የተጣለባቸውን አደራ የሚያመላክትን ሰፊ ውይይት መርተዋል። በውይይቱም በቦታው የተገኙት ደጋፊዎች እና አመራሮች በአሰልጣኞቹ ላይ ያላቸውን ዕምነት በመግለፅ በቀጣዩ የውድድር ዓመት ሁሉም የክለቡ ቡድኖች ወደ ውጤታማነት እንዲመለሱ የበኩላቸውን እንደሚወጡ በመናገር የቅርብ ዓመታት የክለቡ ታሪክ እንዲቀየርም አሰልጣኞችን አደራ ብለዋል።

ክለቡን በአዲስ መልክ የተቀላቀለችው አሰልጣኝ እየሩሳሌም ነጋሽን ጨምሮ በክለቡ ታሪካዊ ዘመናት ላይ በተጨዋችነት ፣ በአሰልጣኝነት እና በሌሎች ኃላፊነት ላይ አገልግለው ያለፉት እና ዳግም ከፍተኛ አደራ ተጥሎባቸው የተሾሙት አሰልጣኞችም በዕውቀት እና በእውነት ለማገልገል ቃል ገብተዋል። ከአንድ ሰዓት በላይ የቆየው ውይይትም በውጤት እጅግ ለወረደው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተስፋን የሚፈነጥቁ ሀሳቦች ተንሸራሽረውበት ተጠናቋል።