ሳላሀዲን በርጌቾ ከዋልያዎቹ ስብስብ ውጭ ሆኗል

የፊታችን ዕሁድ ከሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን ጋር የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታውን የሚያደረረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ ሰላሀዲን በርጊቾን በጉዳት አጥቷል።

በአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከነሀሴ 3 ጀምሮ በሀዋሳ ጥሪ ያቀረበላቸው 28 ተጫዋቾችን በመያዝ ዝግጅቱን በማድረግ ላይ ቆይቶ በስተመጨረሻም ዘጠኝ ተጫዋቾችን ቀንሶ 23 የሚሆኑ የመጨረሻ ተጫዋቾች በመያዝ የፊታችን ዕሁድ ከሴራሊዮን ጋር ቡድኑ ላለበት ጨዋታ ሲዘጋጅ ቆይቷል። ቡድኑ በመጀመሪያው ሳምንት የልምምድ መርሀ ግብር አጥቂው አቡበከር ነስሩን በጉዳት ከስብስቡ ውጭ የነበረ ሲሆን ከቀናት በተቀነሱት ተጫዋቾች ውስጥ አቤል ማሞ፣ በዛብህ መለዮ፣ እስራኤል እሸቱ፣ ተመስገን ካስትሮ እና አወት ገ/ሚካኤል በተመሳሳይ በጉዳት ከስብስቡ ውጭ እንደሆኑ የሚታወስ ነው። አሁን ደግሞ ሴራሊዮንን ለመግጠም የመጨረሻ ዝርዝር ውስጥ የነበረው ሳላሀዲን በርጊቾ በጉዳት ምክንያት ከዋልያዎቹ ስብስብ ውጭ ሆኗል። 

የቡሩንዲ ብሔራዊ ቡድንን በወዳጅነት ጨወታ በገጠመበት ወቅት በ10ኛው ደቂቃ ተጎድቶ የወጣው የመሀል ተከላካዩ ለማገገም በግል ያለፉትን ሶስት ቀናት ሲሰራ ቢቆይም ብቁ ባለመሆኑ ከስብስቡ ውጭ መደረጉን አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል “ሳላሀዲን የብሩንዲ ጨወታ እለት መጠነኛ ጉዳት  ገጠመው። ከዛ በኃላ እንደገና ከቡድኑ ጋር ልምምድ እየሰራ እያለ እዛው ቦታ ላይ ህመም ተሰምቶት አቋርጦ ወጥቷል። የህክምና ቡድኑ የማገገሚያ ልምምዶችን ከሰጠው በኃላ ትላንትም እንደገና ከቡድኑ ጋር ተቀላቅሎ የገባ ቢሆንም ህመሙ ስለተሰማው አልቻለም። ዛሬም እንደገና የመጨረሻውን ሙከራ አደረገ፤ አልቻለም። ስለዚህ ቀሪዎቹ 22 ተጫዋቾች ሁሉም ጤነኛ ስለሆኑ እነሱን እንጠቀማለን።” ብለዋል፡፡ የሳላሀዲን በርጌቾን ጉዳት ተከትሎ አስቻለሁ ታመነ እና ሙጂብ ቃሲም እንደሚጣመሩ ይገመታል፡፡

ብሔራዊ ቡድኑ ዛሬ ልምምዱን ከረፋዱ 4 ሰአት ላይ የሰራ ሲሆኑ ከሀገር ውጭ የነበሩት ጋቶች ፓቶም፣ ኡመድ ኡከሪ፣ ሽመልስ በቀለ እና ቢኒያም በላይ ቡድኑን ተቀላቅለው እየሰሩ ይገኛሉ። ነገ ረፋድ የመጨረሻ ልምምዱን ቡድኑ እንሚሰራም ተገልጿል።

በተያያዘ ዜና ተጋጣሚው የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን 36 የልዑካን ቡድን አባላትን በመያዝ ማክሰኞ ሀዋሳ ገብቶ በሳውዝ ስታር ሆቴል ማረፊያውን ያደረገ ሲሆን ልምምዱንም በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ሲሰራ ቆይቷል። ዛሬ 4 ሰዓት በተመሳሳይ የሰራ ሲሆነ ነገ አመሻሽ 10 ሰዓት የመጨረሻ ልምምዱንም ይሰራል ተብሎ ይጠበቃል።