“የነበረንን የዝግጅት ጊዜ በአግባቡ ተጠቅመናል” የዋልያዎቹ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ2019 የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ሁለተኛ ማጣርያ ጨዋታውን በነገው እለት ሀዋሳ ላይ ከሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን ጋር ያደርጋል። ከነሀሴ ሦስት ጀምሮ በሀዋሳ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየው ብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ለጨዋታው ስላደረጉት ዝግጅት ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። 

እስካሁን ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል?

እንግዲህ አዲስ አበባ ህክምና ለሁለት ቀን ካደረግን ባኋላ ቀጥታ ወደ ሀዋሳ መጥተናል። እዚህም በክልሉ አስተዳደር እና ሮሪ ሆቴል መልካም አቀባበል ተደርጎልናል። በሆቴሉም ያለው መስተንግዶ ሆነ ፋሲሊቲ በጣም ጥሩ ነው። ከዚህ ውጭ የሀዋሳ እና አከባቢዋ ነዋሪ ልምምዶችን እየመጣ ይከታተላል፤ ተጫዋቾቹን ያበረታታል። ይህ በጉ ነገር ነው። ወደ ዝግጅቱ ስንመጣ በሁለት የተከፈለ ነው የመጀመሪያው የአካል ብቃት ላይ ያተኮረ ሲሆን ሁለተኛው የቅንጅት ስራ ነው። ሁለቱን ከጨረስን በኋላ ከቡሩንዲ ጋር ባደረግነው የወዳጅነት ጨዋታ የቡድናችንን ጠንካራ እና ደካማ ጎን እንዲሁም የእያንዳንዱ ተጫዋች ያለውን ወቅታዊ አቋም ለማየት አስችሎናል። ጨዋታው በፌደረሽኑ በኩል ስለተገኘ በጣም የሚያስመስግን ነገር ነው።

ቡድኑ ለረጅም ጊዜ ጨዋታ ካለማድረጉ አንፃር ለሴራሊዮኑ ጨዋታ የነበረው የዝግጅት ጊዜ በቂ ነበር ማለት ይቻላል?

ብሔራዊ ቡድኑ አብሮ አለመስራቱ እና ተበትኖ መቆየቱ ዝግጅት ላይ ተፅዕኖ ፈጥሮል። ነገር ግን በነበረን አጭር ጊዜ ውስጥ በቀን ሁለት ጊዜ እንሰራ ነበር። ከዚህ በተረፈ ግን ተጫዋቾች ስለሚጫወቱት አጨዋወት ከሜዳ ላይ ትምህርት በተጨማሪ በክፍል ውስጥ ስናካሂድ ቆይተናል። የስፖርት ስነ-ልቦና እንዲሁም የስነ-ምግብ ባለሙያ ተመድቧል። እነዚህ ሙያተኞች ከአሰልጣኝ ስብስብ ጋር በመሆን ጥሩ ስራ ሰርተዋል። የነበሩንን የዝግጅት ጊዜያት በአግባቡ ተጠቅመናል። ለሴራሊዮኑ ጨዋታ ያለንን በሙሉ ተጠቅመን ውጤታማ ለመሆን ተዘጋጅተናል ብዬ ነው የማምነው።

በተጫዋቹ ምርጫ ላይ አለመሳተፍዎ ያመጣውን ተፅዕኖ እንዴት ያዩታል? 

ብዙ የሚያሰጋ ነገር የለብኝም። ከሶስት ሳምንት በላይ ስንቆይ የነበረው ተነሳሽነት ከፍተኛነትን አይቻለሁ። በመጀመሪያው ጨዋታ ሽንፈት ቢያጋጥመንም ይህ ጨዋታ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው። ሀገር ውስጥ ከሚገኙት ባለሙያዋች እና ረዳቶቼ ጋር በመተባበር ካየሁቸው ቪድዮች አንፃር የተጫዋች ስብስቡ ጥሩ ነው። ወደፊት በጎደሉ ቦታዎች ላይ እየጠጋገንን ጠንካራ ብሔራዊ ቡድንን እንፈጥራለን። ዋናው አላማ ምንድን ነው ጥቂት ልምድ ያላቸው በርካታ ወጣቶች የያዘ ስብስብን መገንባት ነው።

በየመን ብሔራዊ ቡድን እና በኢትዮጽያ ብሔራዊ ቡድን መካከል ያለውን ልዩነት እንዴት አገኙት?

ኳሱም ሆነ ስልጠናው ያው ነው። ልዩነቱ ሁለቱ ሀገራት ለውድድሮች የሚሰጡት ትኩረት ነው። ካላንደር አጠቃቀም ላይ የየመን ቡድን የፊፋ እና የእስያ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን የሚያወጡትን የወዳጅነት ጨዋታ መርሐ ግብር በአግባቡ ያከናውናል፤እኛ ደሞ አንጠቀምም። ሌላው እነሱ የተሰበሰቡት ሊግ በሌለበት በመሆኑ ለሀገራችን አንድ ታሪክ ሰርተን ማለፍ አለብን ብለው ያስቡ ነበር። ስለዚህም በስነ ልቦናው በኩል በጣም ጠንካራ ናቸው። እኛ ደግሞ የተረጋጋ ሀገር ላይ ነን ያለነው። እነሱ በዛ ውስጥ ሆነው ያንን ካሳኩ የኛ ልጆች ከዛ በላይ ይሰራሉ ብዬ አስባለው። የግል ክህሎት በተመለከተ የሀገራችን ተጫዋቾች ላይ በጣም ጥሩ ነገር ነው ያለው። ጠንክር ያለ ስራ ከተሰራ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን መገንባት የማይቻልበት ምክንያት የለም።

የሴራሊዮን ቡድን ቀደም ብሎ ሀዋሳ መጥቷል። ስለ ቡድኑ የሚያውቁት ነገር አለ?

አዎ፤ ጠንካራ ቡድን ነው። ምዕራብ አፍሪካውያን ጥሩ ቡድን ናቸው፤ ሴራሊዮንም እንደዛው። እኛ ያለንን ጠንካራ ጎን ይዘን በእነሱ ደካማ ጎን ተጠቅመን ለማሸነፍ ነው የምንጥረው። መረጃ በተመለከተ ቡድኑ ከኬንያ ጋር ያደረጉትን ጨዋታ ቪዲዮ ተመልክተናል። ከዚህ ውጭ የምዕራብ አፍሪካ የዞን ውድድር ላይ ከናይጀሪያ ያደረጉት ጨዋታንም አይተናል። በሁለቱ ውድድሮች መካከል የነበረው ዋና ልዩነቱ ከኬንያ ጋር ያደረጉት ጨዋታ ላይ የተሰለፉት ተጫዋቾች በሙሉ ማለት ይቻላል በተለያዩ የዓለማችን ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾች ናቸው። በዞኑ ውድድር ከናይጀሪያ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ግን በሀገር ውስጥ ባሉት ተጫዋቾች ነበር ያደረጉት። በአጠቃላይ ግን የቡድኑ አጨዋወት፣ የትኛው ጠንካራ ጎን የትኛው ደካማ ጎን ነው የሚለውን ለማየት አስችሎናል።

ስለ ተጫዋቾቻቸው ስብስብስ?

ቀደም ብየ እንደገለፅኩት አብዘኛዎቹ ተጫዋቾቻቸው በተለያዩ ሊጎች የሚጫወቱ ናቸው። የጨዋታ ዝግጁነታቸው እና ልምዳቸው ትልቅ ነው፣ የተሻለ ስልጠና ያገኛሉ፣ በስነ-ልቦናው ረገድ ጥሩ ናቸው። ምክንያቱም በተሻሉ ሊጎች ስለሚጫወቱ የተሻለ ክፍያ አላቸው። ነገር ግን በዚህ ረገድ ስብስቡ ችግር ይፈጥርብናል ብዬ አላምንም። ሊጋቸውም ተቋርጦል ብለን አናሳንሳቸውም፤ አናገዝፋቸውም። ነገር ግን ጥሩ ግምት እንሰጣቸዋለን።

በጨዋታው ዙሪያ ለህብረተሰቡ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ይኖራል?

በሀዋሳ እና አካባቢው የሚገኘው መላው የስፖርት አፍቃሪ ወደ ሜዳ መጥቶ እንዲደግፈን እጠይቃለሁ። በወዳጅነት ጨዋታ ፤ እርስ በእርስ ጨዋታዎች እንዲሁም በልምምድ ጊዜ እየመጣ እንዳበረታታን ሁሉ በዋናው ጨዋታ ላይም ስታድየም በመገኘት እንዲደግፈን ጥሪዬን አቀርባለሁ።