” እንደ አዲስ ወደ ፉክክሩ ውስጥ ገብተናል ” የዋልያዎቹ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታው የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድንን አስተናግዶ በጌታነህ ከበደ ብቸኛ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል 1-0 በማሸፍ ከሶስቱ የምድብ ተጋጣሚዎቹ ጋር በነጥብ መስተካከል ችሏል። በሐምሌ ወር በይፋ የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ሆነው የተሾሙት አዲሱ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በመጀመርያ የነጥብ ጨዋታቸውን በድል መወጣት ችለዋል። ከጨዋታው በኋላም ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ከብሩንዲው የወዳጅነት ጨዋታ በኋላ ምን ለውጦች ታይተዋል? በወዳጅነት ጨዋታው ያልነበሩት ከሀገር ውጪ ክለቦች የተመረጡት ተጨዋቾችንስ እንዴት ገመገምካቸው?

ከብሩንዲው ጨዋታ በመነሳት በማጥቃት ላይ የነበረብንን ችግር በመጠኑ አስተካክለናል ብዬ አስባለው። ከሱም በተጨማሪ የተከላካይ መስመሩ የነበረበት የቅንጅት ችግርን ዛሬ ተስተካክሏል። ነገር ግን አሁንም የማጥቃት ክልል ውስጥ ስንገባ የምናባክናቸው ኳሶች አልተስተካከሉም። ቢሆንም ኳሱን ተጫውተን ተጋጣሚ ጎል ክልል ላይ የመድረሳችንን ነገር እንደ ጥሩ አየዋለው። ሁሉም ሰው እንደተመለከተው ጨዋታውን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥረን ነው የጨረስነው። ይህ ደግሞ በተጨዋቾቹ ስነ ልቦና ላይ መልካም ነገር ይፈጥራል። በውጪ ሃገር የሚጫወቱ ተጨዋቾችን በተመለከተ ሁሉም የአቅማቸውን ሰርተዋል፤ ነገር ግን መጠነኛ የቅንጅት ችግር ነበር። ይህ ደግሞ የሆነ ከሌሎች ተጨዋቾች ጋር በደንብ ልምምዶችን ስላልሰሩ ነው። ነገር ግን ወደፊት ተደጋጋሚ ልምምዶችን ሲሰሩ እና የአጨዋወት መንገዱን ሲረዱት ከዚህ የተሻለ ነገር ያመጣሉ ብዬ አስባለው። አልፎ አልፎ ኳስ ሲበላሽባቸው የነበረው ለሃገራቸው ድል ለማምጣት ከፍተኛ ጉጉት ስለተፈጠረባቸው ነው።

በዛሬው ጨዋታ በ4-2-3-1 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ገብታችኋል። ከተከላካዮቹ ፊት የተጣመሩት ጋቶች እና ሙሉዓለም እንደምትፈልገው ተጫውተውልሃል?

አዎ በጣም በጥሩ ሁኔታ የተሰጣቸውን በሚገባ ተግብረዋል። አልፎ አልፎ ጋቶች ከጉጉት የተነሳ ኳሶች ሲበላሹበት ነበረ። እኔ ከሁለቱ የፈለኩት ቡድኑ በተደጋጋሚ ሽንፈቶችን ሲያስተናግድ የቆየ እንደመሆኑ ለተከላካዮች ተገቢ ሽፋን በመስጠት እና የአማካይ ክፍሉን በቁጥር በርከት በማድረግ ኳሶችን ተጫውተን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ነው። እነሱም ደግሞ ከጨዋታው በፊት የተሰጣቸውን ነገር በሚገባ ሜዳ ላይ ተግብረዋል።

ከአጥቂ ጀርባ የነበሩት ተጨዋቾች በዛሬው ጨዋታ ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል። ነገር ግን የማጥቃት ወረዳው ላይ ሲደርሱ ሲደርሱ ደካማ እንቅስቃሴ ሲያሳዩ እና የስልነት ችግር ሲስተዋልባቸው ነበር። በቀጣይ ጨዋታ ይህንን ችግር በምን መልኩ ለማስተካከል አስበሀል?

በቀጣይ ልዩ ልምምዶችን እየሰራን የአጨራረስ ብቃታችንን ለማስተካከል እንሞክራልን። ይሄ ችግር ለረጅም ጊዜ ከብሄራዊ ቡድናችን ጋር የቆየ ችግር ነው። ስለዚህ ከፍተኛ ስራ ይጠይቃል፤ ይህንንም ደግሞ ለማስተካከል እንጥራለን።

2010ን በድል አጠናቃችኋል። በቀጣይ ወር ደግሞ ሶስተኛ የምድብ ጨዋታችሁን ከኬንያ ጋር ታደርጋላችሁ። የዛሬው ውጤት ምን ያህል ተነሳሽነት ይፈጥራል ብለክ ታስባለህ?

በጣም ተነሳሽነት ይፈጥርልናል። አሁን እኮ ምድብ ውስጥ ያሉት ሁሉም ቡድኖች እኩል ነጥብ ነው ያላቸው። ይህ ደግሞ ውድድሩን እንደ አዲስ መጀመር ማለት ነው። እንደ አዲስ ወደ ፉክክሩ ውስጥ ገብተናል፣ የማለፍ ተስፋችንም እንደ እንደ አዲስ አለምልሟል ማለት ነው። ይሄ ደግሞ በተጨዋቾች ስነ ልቦና እና የራስ መተማመን መንፈስ ላይ የዛሬው ድል ትልቅ ትርጉም አለው። አዲሱን ዓመት ደግሞ በደስታ እንድናሳልፍ ትልቁን ክሬዲት ተጨዋቾቼ ይወስዳሉ። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ረዳቶቼ ከፍተኛ ምስጋና ይገባቸዋል። ተጨዋቾቹም ሲመረጡ ድጋፍ ላደረጉልኝ የሃገራችን አሰልጣኞች ምስጋና ይገባል።