አዲስ አበባ ከተማ የቴክኒክ ዳይሬክተር እና የሴት ቡድን አሰልጣኝ ቀጥሯል

የከፍተኛ ሊጉ ክለብ አዲስ አበባ ከተማ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ወደ አንደኛ ዲቪዝዮን ላደገው የሴቶች ቡድኑ አሰልጣኝ ሲቀጥር የቴክኒክ ዳይሬክተርም ሾማል። ክለቡ በቀጣይ ቀናት ለወንዶች ቡድኑ አዲስ አሰልጣኝ እንደሚሾምም ይጠበቃል።

መሰረት ማኒ አዲሷ የአዲስ አበበ ከተማ ሴቶች ቡድን አሰልጣኝ ሆና ለቀጣዮቹ ሁለት የውድድር ዓመታት የምትመራ ይሆናል። የቀድሞዋ የድሬዳዋ ከተማ ወንዶች ቡድን እና የሉሲዎቹ አሰልጣኝ መሰረት ከብሔራዊ ቡድን ከተለያየች በኋላ በታዳጊዎች ስልጠና ላይ ስትሰራ የቆየች ሲሆን አዲሱን የውድድር ዘመን ወደ አንደኛ ዲቪዝዮን ባደገው የዋና ከተማው ክለብ የምንመለከታት ይሆናል። መሠረት በ2007 ድሬዳዋ ከተማን ለፕሪምየር ሊግ በማብቃት በታሪክ የመጀመርያዋ ሴት የፕሪምየር ሊግ ክለብ አሰልጣኝ በመሆን ታሪክ መስራቷ የሚታወስ ነው። 

ከለቡ በቴክኒክ ዳይሬክተርነት የቀጠረው ዳንኤል ገብረማርያምን ነው። አቶ ዳንኤል በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቴክነክ ዲፓርትመንት ውስጥ የሰሩ ሲሆን ለአጭር ጊዜም የቴክኒክ ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል። የተጠኔቀቀው የውድድር ዓመትን ደግሞ በአዳማ ከተማ አሳልፈዋል። አቶ ዳንኤል እንደ መሠረት ሁሉ የሁለት ዓመት ውል እንደተሰጣቸው ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። 

በከፍተኛ ሊግ የሚወዳደረው የአአ ከተማ ወንዶች ቡድን በ25ኛው ሳምንት ከአሰልጣኙ አስራት አባተ ጋር ከተለያየ በኋላ ዋና አሰልጣኝ ሳይቀጥር የቆየ ሲሆን መኮንን ገብረዮሀንስን አሰልጣኝ አድርጎ ለመሾም መቃረቡ ታውቋል። አሰልጣኝ መኮንን ከዚህ ቀደም ከዳሽን ቢራ፣ ኢትዮጵያ ውሀ ስፖርት እና ጅማ አባ ጅፋርን ወደ ፕሪምየር ሊግ ማሳደግ ችለዋል።