የአአ ከተማ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሲቲ ካፑን ለመጀመር ያሰበበትን ቀን አሳውቋል

የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌደሬሽን በየዓመቱ የሚያዘጋጀው የሲቲ ካፕ ውድድር ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ እንደሚከናወን ይጠበቃል። ፌደሬሽኑም ውድድሩን ለማከናወን ያሰበበትን ቀን ይፋ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከመጀመሩ በፊት የክልል ፌደሬሽኖች የሚያዘጋጇዋቸው የሲቲ ካፕ ውድድሮች ዘንድሮም ሲከናወኑ ከሳምንት በፊት የፕሬዝዳንት እና የስራ አስፈፃሚ የሟሟያ ምርጫውን ያደረገው የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከምርጫው በኃላ ውድድሩ በደመቀ ሁኔታ እንዲከናወን ስራዎችን እየሰራ ይገኛል።

ሶከር ኢትዮጵያ ከፌደሬሽኑ ባገኘችው መረጃ መሰረት ከጥቅምት 3-18 ድረስ በአዲስ አበባ ስታዲየም ውድድሩ ለማከናወን ፌዴሬሽኑ እንዳሰበ የገለፀ ሲሆን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጥቅምት 17 ይጀመራል ብሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ካስቀመጠው ቀን ጋር ተጋጭቷል። ይህንን ተከትሎ ለአዲሱ የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኢ/ር ኃይለየሱስ ፍስሃ ለሶከር ኢትዮጵያ ይህን ብለዋል። “እኛ ያሰብነው ውድድሩን ከጥቅምት 3-18 ለማድረግ ነው። ይህንን ደግሞ የወሰንነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን መስከረም 30 አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ጨዋታ ያደርጋል እየተባለ ስለሆነ ሜዳው ስለሚያዝብን ነው። ያለን አማራጭ ከብሄራዊ ቡድኑ ጨዋታ በኋላ ውድድራችን ማድረግ ነው።” ብለዋል። በመቀጠል ከፌደሬሽኑ ጋር ድርድር አድርጋችኋል ወይ የሚለውን ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ፕሬዝዳንቱ”ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጋር ለመደራደር ሰኞ ቀጠሮ ይዘናል። በምንችለው አቅም ፌደሬሽኑ ፕሪምየር ሊጉን የሚጀምርበትን ቀን እንዲቀይር ለማሳመን እንሞክራለን። ካለሆነ እና የማይቀየር ነገር ከሌለ ግን ከጥቅምት 1-14 ውድድሩን ለማከናወን እንገደዳለን” ብለዋል።

ተሳታፊ ክለቦችን በተመለከተ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ የሚሳተፉት ሶስቱ የአዲስ አበባ ክለቦችን (መከላከያ፣ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ) እንዲሁም ተጨማሪ የሃገር ውስጥ እና የምስራቅ አፍሪካ ተጋባዥ ክለቦችን በውድድሩ ተሳታፊ እንዲሆኑ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ተብሏል። ከተጋባዥ የሃገር ውስጥ የአዲስ አበባ ክለቦች ውስጥ ዘንድሮ ወደ ከፍተኛ ሊግ የወረደው ኢትዮ ኤሌክትሪክ አልያም አምና በከፍተኛው ሊግ ሲወዳደር ቆይቶ  አምስተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ወደ ፕሪምየር ሊግ የማደግ አላማውን ሳያሳካ የቀረው አዲስ አበባ ከተማን በውድድሩ ለማሳተፍ እንዲሁም ከክልል ተጋባዥ ክለቦች ውስጥ ደግሞ ከፋሲል ከተማ፣ከወላይታ ዲቻ፣ከጅማ አባጅፋር እና ከአዳማ ከተማ ውስጥ የተስማሙ ክለቦችን ለመጋበዝ በአጠቃላይ በስምንት ቡድኖች መካከል ውድድሩን ለማድረግ እንደታሰበ ተነግሯል።