የግርማ ታደሰ ውዝግብ – አሰልጣኙ የደቡብ ፖሊስ ወይስ የሀዲያ ሆሳዕና ?

ደቡብ ፖሊስን ከስምንት ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመለሱት አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ባሳለፍነው ሳምንት ከክለቡ ጋር ለመቀጠል መስማማታቸው የተነገረ ቢሆንም ሀዲያ ሆሳዕና ለክለባቸው እንደፈረሙ አረጋግጧል። አሰልጣኙ ደግሞ ከሁለቱም ወገን ጋር ስምምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል። 

አሰልጣኙ ባለፉት ጥቂት ቀናት በደቡብ ፖሊስ የማይገኙ ሲሆን በጉዳዩ ዙርያ ያላቸውን ሀሳብ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል። ደቡብ ፖሊስ እና ሀዲያ ሆሳዕናም ምላሻቸውን ሰጥተውናል።  

አሰልጣኝ ግርማ ከክለቡ ጋር የማይቀጥሉበትን ምክንያት ለሶከር ኢትዮጵያ እንዲህ አብራርተዋል። “አዎ ከደቡብ ፖሊስ ጋር ለመቀጠል ተስማምተን ነበር። ነገር ግን ሰሞኑን እናቴ ስለታመመች እና ከፍተኛ ክትትል ስለምትሻ ከጎኗ ሆኜ ማገዝ እንዳለብኝ በማመኔ ከፖሊሶች ጋር የነበረኝን ስምምነት ለማንሳት ተገድጃለው። አሁን ባለሁበት ሁኔታ እኔ ሙሉ ጉልበቴን እና እውቀቴን በትኩረት ለክለቡ መስጠት አልችልም እነሱ ደግሞ ይህንን መረዳት አለባቸው። ጊዜው በጣም እየሄደ ስለሆነ እና የቤተሰቤ ነገር ጊዜ ስለሚወስድ ክለቡን ለመልቀቅ ተገድጃለው። እንደ አሰልጣኝ ደግሞ በከፍተኛ ሊጉ የሰራሁትን ጥሩ ነገር በማይሆን ነገር መናድ እና ማፍረስ አልፈልግም። ስለዚህ ይህንን ውሳኔ ወስኛለው።” ብለዋል።

ለጥያቄዎች ምላሽ መስጠታቸውን የቀጠሉት አሰልጣኝ ግርማ ከደቡብ ፖሊሶች ጋር ለመለያየት መወሰናቸውን ለክለቡ አመራሮች ስለማሳወቃቸው እና ስለ ውላቸው ይህንን ምላሽ ሰተዋል። “ለክለቡ አመራሮች ውሳኔዬን በአጭር የፅሁፍ መልዕክት (SMS) ጨምሮ በስልክ በመደወል አሳውቄያቸዋለው። ትላንት እና ከትላንት በስትያ ስልኬ ስለተበላሸ ነው እንጂ በተደጋጋሚ ከአመራሮቹም ጋር ከምክትሎቼም ጋር መልዕክቶችን ስንለዋወጥ ነበር። እውነት ለመናገር ክለቡ ከፍተኛ ችግር ያለበት ክለብ ነው፤ ዘንድሮ ብዙ ችግሮች ነበሩብን። እኔ እና ልጆቼ ብዙ ታግለን ነው ለፕሪምየር ሊጉ የበቃነው። የነበሩብን ችግሮች ሳይስተካከሉ ቀጣይ ነገር ማቀድ በጣም ከባድ ነው። እንደ አጋጣሚ የማይቀየር የቤተሰብ ችግር ሆነብኝ እንጂ እሱም ባይሆን እንኳ ከክለቡ ጋር መቆየት ከባድ ነው። ውሉን በተመለከተ ከስምምነት በቀር ከክለቡ ጋር ምንም ይፋዊ ውል የለንም፤ ስለዚህ ውል አለው የሚባለው ነገር ውሸት ነው። ክለቡ ከዚህ በኋላ ስለ እኔ ማሰብ አቁሞ ቀጣይ የክለቡን አሰልጣኝ የመሾም ጉዳይ ላይ ትኩረቱን ማድረግ አለበት።”

በመጨረሻም ስለቀጣይ ማረፊያቸው የተናገሩት አሰልጣኙ “አሁን ማሰብ የምፈልገው ስለቤተሰቤ ብቻ ነው። ሃዲያ ሆሳዕናዎች ሃዋሳ ድረስ በመምጣት አናግረውኝ ነበር። ነገር ግን አሁን ያለሁበት ወቅታዊ ሁኔታ ምንም ነገር እንዳስብ አያደርገኝም። ስለዚህ ከማንም ክለብ ጋር አልተፈራረምኩም።” ብለዋል።

የክለቡ ፕሬዝዳንት ኮማንደር ዳንኤል ገዛኸኝ በበኩላቸው አሰልጣኙ ከክለባቸው ጋር እንደሚቀጥል ብቻ እንደሚያውቁ ገልፀዋል። “በከፍተኛ ሊጉ ውድድር ማብቂያ ሰሞን ስለ ቀጣዩ ዓመት ሰፊ ውይይት አድርገን በተጫዋች መረጣ እና ምልመላ ላይም አብረን ስንሰራ ነው የቆየነው። እኔ እስካለኝ መረጃ አሰልጣኙ ከክለቡ ጋር ውል እንዳለው እና እንደሚቀጥል ነው የማውቀው። ከዛ ውጪ በተለያዩ የሚድያ አውታሮች የሚወሩት እና የሚጠይቁኝ ነገሮችም እኔ የማውቃቸው አይደሉም። እንደ ህግ ስንሄድ ደግሞ ፌዴሬሽኑ ባስቀመጠው ደንብ መሰረት የውል ግዴታዎቻችንን እንደምንፈፅም ነው የምንረዳው። ስላለመቀጠሉ ከማንኛውም ኃላፊ ጋር ንግግር አድርጎ አያውቅም። ወላጅ እናቱ ታመው በዛ ምክንያት ከክለቡ እንደራቀ ነው መረጃው ያለኝ። ከሱ ጋር አንቀጥልም የምንልበት ጉዳይ የለም። የማይቀጥልበት አስገዳጅ ሁኔታ ቢኖር እንኳን ሊያሳውቀን ይገባል። አሰልጣኞች የራሳቸው ፍላጎት ሊኖር ይችላል። እንደ ክለብ ደግሞ በህግ እና ደንብ ነው ልንመራ የምንችለው። ስለዚህ ጉዳያችን በስምምነት ብቻ ነው ሊቋጭ የሚችለው። ለዚህ ደግሞ ኦፊሻል ሆኖ የቀረበ ነገር በሌለበት ሁኔታ አሰልጣኙ ከኛ ጋር ያለውን ነገር አቋርጧል ብለን መናገር አንችልም። ” ብለዋል።

አሰልጣኝ ግርማ በክለቡ አካባቢ ባይኖሩም ደቡብ ፖሊስ ተጫዋቾችን በማዘዋወር ላይ ይገኛል። ያለ አሰልጣኙ ተሳትፎ ዝውውሮች መከናወናቸውን በተመለከተም ስራ አስኪያጁ የሚከተለውን ብለዋል። ” የተጫዋቾች መረጣ ጉዳይ ከዚህ ቀደም ከአሰልጣኙ ጋር የተካሄደ ነው። የሚቀጥሉት እና አዳዲስ የሚመጡት ቀድሞ ተወስኗል። ስለዚህ ስራችን እነሱን አግባብቶ ማስፈረም ነው የሚሆነው። እሱ ከለቀቀ የሚሆነውን ወደ ፊት አብረን እናያለን፤ አሁን ግን በእቅዳችን መሰረት ነው እየተጓዝን ያለነው። ” ብለዋል። አሰልጣኙ ከሌላ ክለብ ጋር ከተስማሙም በህግ አግባብ ጉዳዩን እንደሚመለከቱት በመግለፅ ሀሳባቸውን አጠቃለዋል።

የሀዲያ ሆሳዕና ስራ አስኪያጅ አቶ መላኩ አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ለክለባቸው እንደፈረመ ለሶከር ኢትዮጽያ ገልፀዋል። ” ግርማ ታደሰ ለኛ ፊርማውን አኑሯል። ከአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ጋር በስምምነት ለመለያየት ከወሰንን በኋላ ግርማን ወደ ክለባችን ለማምጣት ተስማምተን በዕለተ ማክሰኞ ፊርማውን አኑሮልናል። ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንም ስምምነታችንን አስገብተናል። ስለዚህ ግርማ በ2011 ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር እንደሚቆይ ነው የማውቀው።” ብለዋል። ሶከር ኢትዮጽያ ከፌዴሬሽኑ ባደረገው ማጣራት ሀዲያ ሆሳዕና ከግርማ ጋር ያደረገው ስምምነት የገባ ቢሆንም ለማፅደቅ ግን ከክፍሌ ቦልተና ጋር በስምምነት መለያየታቸውን የሚገልፅ ደብዳቤ ይዘው መምጣት ስለሚጠበቅባቸው እስካሁን አልፀደቀም።

አሰልጣኝ ግርማ ለሀዲያ ሆሳዕና መፈረማቸውን ተከትሎ በቀጣይ የደቡብ ፖሊስ እርምጃ ምን ይሆናል? ክለቡ እንደሚለው አሰልጣኙ ውል አላቸው? ወይስ አሰልጣኝ ግርማ እንደሚሉት ይፋዊ ውል የላቸውም? የሚለው የሚጠበቅ ጉዳይ ነው።