የትግራይ ዋንጫ የሚካሄድበት ቀን ታውቋል

የትግራይ እግር ኳስ ፌደሬሽን የክልሉ ክለቦች እና ተጋባዦችን የሚያሳትፍ ውድድር የሚያካሄድበትን ቀን አሳውቋል። 
ውድድሩ መስከረም 12 ይጀመራል ተብሎ ቢጠበቅም ሶከር ኢትዮጵያ ከፌደሬሽኑ ባገኘችው መረጃ መሰረት በአንድ ሳምንት ተራዝሞ ከመስከረም 19-26 ድረስ በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታድየም ለማከናወን ከውሳኔ ላይ ተደርሷል። ውድድሩን ለመጀመር ከታሰበበት ጊዜ በአንድ ሳምንት ለማራዘም ያስፈለገበት ምክንያት ሽረ እንዳስላሴ የከፍተኛ ሊግ ውድድርን ዘግይቶ በማጠናቀቁና ዝግጅት የሚጀምርበት ጊዜን የሚያዘገየው በመሆኑ እነደሆነ ተገልጿል።

ተሳታፊ ክለቦችን በተመለከተ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ የሚሳተፉት አራቱን የትግራይ ክለቦች (መቐለ ከተማ፣ ደደቢት፣ ወልዋሎ እና ሽረ) እንዲሁም የከፍተኛ ሊጉ ክለብ አክሱም ከተማ የሚካፈሉበት ሲሆን በተጋባዥነት ደግሞ ቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በመቐለ እያከናወነ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል። በቀጣይ ቀናት ሌሎች ተጋባዥ ክለቦች ሊኖሩ እንደሚችሉም ፌዴሬሽኑ ገልጿል።