አብዱልከሪም መሐመድ እና ሰናይት ቦጋለ የኢቢሲ የዓመቱ ኮከቦች ሆነው ተመርጠዋል

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (EBC) ለሁለተኛ ጊዜ ያከናወነው “የኢቢሲ ስፖርት ሽልማት” ዛሬ ምሽት በሸራተን አዲስ ሆቴል ሲካሄድ በአምስት የተለያዩ ዘርፎች ለተወዳደሩ እጩ ተወዳዳሪ አሸናፊዎች ሽልማት አበርክቷል።

ለሁለተኛ ጊዜ በተከናወነው በዚህ የሽልማት ፕሮግራም አምና በአራት ዘርፎች ብቻ መከናወኑ የሚታወስ ሲሆን ዘንድሮ የህይወት ዘመን ተሸላሚ የሚል ዘርፍ በመጨመር በአጠቃላይ በአምስት ዘርፎች ለአሸናፊዎች ሽልማት ተበርክቷል። ወጣት ስፖርተኞችን ለማበረታታት፣ ተሸላሚ ስፖርተኞች ዘንድ መነቃቃት እንዲፈጠር፣ የስፖርት ቤተሰቡ ለሀገር ውስጥ ስፖርት ያለው ግንዛቤ እና ተሳትፎ ከፍ እንዲል ለማድረግ የሚሉ አላማዎችን በመያዝ የሚዘጋጀው ይህ የሽልማት ፕሮግራም በተለይ የተቋሙን የማህበራዊ ኃላፊነት ከመወጣት ጎን ለጎን ታዳጊዎች እንዲበረታቱ ታስቦ እንደሚሰራ መጠቆሙ ይታወሳል።

12:15 ሲል በጀመረው ፕሮግራም የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚንስትር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት አሸብር ወ/ጊዬርጊስ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ኢሳያስ ጂራ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ኃይሌ ገ/ስላሴ (ሻለቃ አትሌት) ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው 2000 እንግዶች በላሊበላ አዳራሽ የተገኙ ሲሆን ዝግጅቱ ከመጀመሩ በፊት ለእንግዶቹ  በቀይ ምንጣፍ የታጀበ አቀባበል እና የፎቶ መነሳት ስነ-ስርዓት ተከናውኗል።

እንግዶቹ ወደ አዳራሽ ከገቡ በኋላ በሁሉም ዘርፍ (የህይወት ዘመን ተሸላሚ የሚለውን ዘርፍ ሳይጨምር) ለተወዳደሩ የመጨረሻ ሶስት እጩ  ስፖርተኞች አቀባበል የተደረገ ሲሆን እጩዎቹ በዓመቱ ስላሳለፉት ጊዜም ገለፃ ተደርጓል።

ከአምስቱ ዘርፎች በመጀመሪያ ምርጥ ሴት የእግር  ኳስ ተጨዋች አሸናፊ ይፋ ሲደረግ በ2004 የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ አራተኛ ደረጃ ይዞ ሲያጠናቅቅ የቡድኑ አባል የነበረችው እና ከረጅም ዓመታት በኋላ በ2009 የህክምና ትምህርቷን አጠናቃ ዳግም ወደ እግር ኳስ በአዳማ ከተማ ማልያ የተመለሰችው እንደገና አለምዋሶ (ዶ/ር) ከደደቢቷ ሎዛ አበራ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ህይወት ደንጊሶ እና ከደደቢቷ ሰናይት ቦጋለ አሸናፊዋን አብስራለች።

ከሶስቱ እጩ ሴት እግር ኳስ ተጨዋቾች ለሁለተኛ ጊዜ የተከናወነውን “የኢቢሲ የስፖርት ሽልማት” አሸናፊ የሆነችው የደደቢቷ የመሃል ሜዳ ተጨዋች ሰናይት ቦጋለ ሆና ተመርጣለች። ተጨዋቿም የዋንጫ እና የ75ሺ ብር ሽልማቷን ከእንደገና አለምዋሶ ከተረከበች በኋላ የተሰማትን ስሜት ለታዳሚያኑ አጋርታለች። “በመጀመሪያ ሰሞኑን ሀገራችን ላይ  በተፈጠረው ነገር በጣም አዝኛለው። ለሞቱት ነብሳቸው በገነት ያኑርልን ለቆሰሉት እና ለተጎዱት ደግሞ ፈጣሪ ምህረትን ይስጥልኝ። በማሸነፌ በጣም ተደስቻለው። ከምንም በላይ ለዚህ ላበቃኝ ለፈጣሪዬን ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለው። ከዛ በመቀጠል ሁሌ ከጎኔ ሆነው ለደገፉኝ ቤተሰቦቼ ትልቅ ክብር አለኝ። አምናም እጩ ተጨዋቾች ውስጥ ስሜ ሲገባ ሲደግፉኝ እና ሲያበረታቱኝ ነበረ። ዘንድሮም ከአጠገቤ ሆነው ስለነበረ ምስጋና ይድረሳቸው።” በማለት አስተያየቷን አካፍላ በማሸነፏ ደስተኛ መሆኗን ገልፃለች።

ከምርጥ ሴት እግር ኳስ ተጨዋች አሸናፊ በኋላ ምርጥ ወንድ እግር ኳስ ተጨዋች አሸናፊ ይፋ ሆኗል። አሸናፊውን ይፋ ያደረጉት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ሰውነት ቢሻው (ኢንስትራክተር) ሲሆኑ ከኢትዮጵያ ቡናው አማኑኤል ዩሃንስ፣ ከጅማ አባጅፋሩ ሄኖክ አዱኛ እና ከቅዱስ ጊዮርጊሱ አብዱልከሪም መሃመድ መካከል አሸናፊውን አሳውቀዋል። ከነዚህ ሶስት እጩዎች በቅዱስ ጊዮርጊስ ማልያ ዓመቱን ያሳለፈው የቀኝ መስመር ተከላካዩ አብዱልከሪም መሃመድ አሸናፊ ሆኖ ሽልማቱን ከኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ተቀብቧል። ተጨዋቹም የዋንጫ እና የ75ሺ ብር  ሽልማቱን ከተቀበለ በኋላ በዓመቱ ጥሩ ጊዜ እንዲያሳልፍ ለረዱት ግለሰቦች እና አካላት ምስጋና አቅርቧል። “ከሁሉም በላይ ፈጣሪዬን ማመስገን እፈልጋለው። ከዛ በመቀጠል ደግሞ በግሌ በአመቱ ጥሩ ጊዜ እንዳሳልፍ ለረዱኝ የክለቤ አባላት ምስጋና እንዲቸራቸው እፈልጋለው። የክለብ አጋሮቼ ባይኖሩ እና ባይረዱኝ ኖሮ ኮከብ ሆኜ ለመሸለም አልችልም ነበር። ከክለብ አጋሮቼ ጎን ለጎን ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ደጋፊዎች በጣም ሲደግፉኝ እና ሲያበረታቱኝ ነበርና ለነሱም ምስጋናዬ ይድረሳቸው።” ብሏል።

በመቀጠል የወንድ ምርጥ አትሌት ዘርፍ አትሌት ሰለሞን ባረጋ ሆኖ የተመረጠ ሲሆን የሴት ምርጥ አትሌት ዘርፍ ደግሞ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ አሸናፊ ሆና ተመርጣለች።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን(EBC) አምና በሁለት የስፖርት አይነቶች ለሁለቱም ፆታዎች ሽልማት መስጠት መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የህይወት ዘመን ተሸላሚ በሚል ዘርፍ ለመረጣቸው ግለሰብ ሽልማት አበርክቷል። በዚህ ዘርፍ አሸናፊ ሆነው የተመረጡት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ በርካታ ስራዎችን የሰሩት አቶ ስንታየው እሸቱ ሲሆኑ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ስዩም መኮንን የዋንጫ እና የ50ሺ ብር ሽልማታቸውን ተረክበዋል።

ዝግጅቱ ከማብቃቱ በፊት የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚንስትር አቶ ርስቱ ይርዳው ስለ ዝግጅቱ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። አቶ ርስቱ በአስተያየታቸው ኢቢሲ ለሁለተኛ ጊዜ ያዘጋጀው ይህ የሽልማት ዝግጅት በጣም ጥሩ መሆኑን ገልፀው መቋረጥ እንደሌለበት እና ቀጣይነት እንዲኖረው አሳስበዋል። አቶ ርስቱ ቀጥለውም በሚኒስቴር መስራቤታቸው ስም ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዝግጅቱን በደመቀ እና ባማረ ሁኔታ ስላዘጋጀው ምስጋና አቅርበዋል።