የትግራይ ክልል ዋንጫን በተመለከተ መግለጫ ተሰጠ

ማክሰኞ መስከረም 08 ቀን 2011

ከአስር ቀናት በኋላ እንደሚጀመር በሚጠበቀው የትግራይ ዋንጫ ዙሪያ ማክሰኞ 9፡00 ላይ በፕላኔት ሆቴል መግለጫ ተሰጥቷል።

ከመስከረም 19 እስከ 26 በሽቶ ሚድያ እና ኮሚውኒኬሽን እና በትግራይ ክልል እግር ኳስ ፌደሬሽን በጣምራ የሚዘጋጀው የትግራይ ክልል ዋንጫን አስመልክቶ ዛሬ 9:00 ሰዓት ላይ በፕላኔት ሆቴል በዝርዝር ጉዳዮች ዙሪያ ያጠነጠነ መግለጫ ተሰጥቷል። አራቱ በትግራይ ክልል የሚገኙ የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች እና የከፍተኛ ሊጉን አክሱም ከተማን ጨምሮ 8 ክለቦች እንደሚያሳትፍ የተገለፀው ይህ ውድድር ድሬዳዋ ከተማ እና መከላከያን እንደሚጨምር ማረጋገጫ እንደተገኘ በመግለጫው ተነግሯል። ከዚህ በተጨማሪ ለሲዳማ ቡና ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ አዳማ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ግብዣ መቅረቡ የተገለፀ ሲሆን ቀድመው በጎ ምላሽ የሰጡ ክለቦች በውድድሩ የሚካተቱ ይሆናል።

በፕሮግራሙ ላይ የውድድሩ መዘጋጀት ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው የገለፁት አዘጋጆቹ በዋነኝነት ክለቦቹ የሜዳ ላይ ብቃታቸውን ለመገምገም የሚያስችላቸው መሆኑ ፣ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እና የገንዘብ አቅማቸው ለማጎልበትም የታለመ እንደሆነ አስረድተዋል። ከአስር ቀናት በኋላ ለሚጀምረው ለዚህ ውድድር በዳኝነት ፣ በፀጥታ እና በትኬት አቆራረጥ ሂደት ላይ በቂ የቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ በመግለጫው የተነሳ ሲሆን  ውድድሩን በገንዘብ ለማጠናከርም አዘጋጆቹ ተጨማሪ ስፖንሰሮች እየተፈለጉ እንደሆነ ተገልጿል።