ጅማ አባ ጅፋር ሁለት ተጨዋቾችን አስፈርሟል

ማክሰኞ መስከረም 8 ቀን 2011

የሊጉ ቻምፒዮን ጅማ አባ ጅፋር ተጨማሪ ተጨዋቾችን ከሽረ እንደስላሴ አምጥቷል።

የመጀመሪያ ተሳትፎው የነበረውን የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዓመት በበላይነት ማጠናቀቅ የቻለው ጅማ አባ ጅፋር አብዛኞቹን ተጨዋቾቹን በዝውውር መስኮቱ ቢያጣም ምትኮቻቸውን ወደ ቡድኑ እየቀላቀለ ይገኛል። እስካሁን ድረስ 11 ተጨዋቾችን ማስፈረም የቻለው ክለቡ ከሻምፒዮንነት በኋላ ከባድ እንደሚሆን የሚገመተው ሁለተኛ የውድድር ዓመትን በብቃት ለመወጣት አሁን ደግሞ ሌሎች ሁለት የሽረ እንደሥላሴ ተጨዋቾችን በእጁ አስገብቷል።

ከአዳዲሶቹ ፈራሚዎች መካከል ከሽረ እንዳሥላሴ ጥሩ የውድድር ዓመት ያሳለፈው ልደቱ ለማ አንደኛው ነው። የቀድሞው የለገጣፎ አጥቂ በውድድር ዓመቱ መጀመርያ ሽረ እንዳሥላሴን ተቀላቅሎ መልካም የውድድር ዓመት ማሳለፍ የቻለ ሲሆን 12 ጎሎችን በማስቆጠር የቡድኑ እና የምድብ ሀ (በጣምራ) ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ዓመቱን አገባዷል። ተጫዋቹ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ከስምምነት ከደረሰ ሳምንታት ቢያስቆጥርም በከፍተኛ ሊጉ ወሳኝ ጨዋታዎች እያደረገ የነበረ በመሆኑ ዝውውር ይፋ ሳይሆን ቆይቷል።

ሌላው የአባ ጅፋር ፈራሚ ደግሞ ብሩክ ገብረዓብ ነው። ብሩክ ለአንድ ዓመት ወልዋሎ ዓ.ዩን ካገለገለ በኋላ ሽረ እንደስላሴን በመቀላቀል ያለፉት ሁለት የውድድር ዓመታትን ቆይቶ ነው ወደ ምዕራቡ ክለብ ያቀናው። ተጨዋቹ  በአማካይ እና በአጥቂ ስፍራ ላይ በመጫወት ነበር ያሳለፍነውን የከፍተኛ ሊግ ውድድር ከክለቡ ጋር በውጤታማነት ያገባደደው።

ዋናኛ ተመራጮቹ የነበሩት ኦኪኪ አፎላቢ እና ተመስገን ገ/ኪዳንን እንዲሁም ከተጠባባቂነት በመነሳት ሲያገለግሉት የቆዩትን ሳምሶን ቆልቻ እና እንዳለ ከበድን በሙሉ ያጣው ጅማ አባ ጅፋር በቦታው የነበረበትን ክፍተት ሳይሸፍን ቆይቷል። እስካሁን በፈፀማቸው ዝውውሮች በሌሎቹ የቡድኑ ክፍሎች ላይ ትኩረት ያደረገው ክለቡ በሁለቱ ተጨዋቾች መምጣት ለአሰልጣኝ ዘማሪያም ወ/ጊዮርጊስ የፊት መስመር አማራጮችን መፍጠር ችሏል።