የአዲስ አበባ ዋንጫ የሚጀምርበት ቀን ተሸጋሽጓል

ረቡዕ መስከረም 9 ቀን 2010

የአዲስ አበባ ዋንጫ ለ13ኛ ጊዜ የሚከናወን ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት ፌደሬሽኑ ውድድሩን ለማከናወን ያሰበበት ቀን ይፋ ካደረገበት የጊዜ ሰሌዳ ለውጦችን ተድርጓል።

አዲስ ፕሬዝዳንት የሾመው ፌደሬሽኑ ከዚህ ቀደም ከጥቅምት 3-18 ውድድሩን ለማከናወን መወሰኑ ነገር ግን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ጥቅምት 17 እጀምራለው ብሎ በማስታወቁ የጊዜ ግጭቶችን በመፍጠሩ ሁኔታውን እንደገና እንዲጤን እንዳደረገው ተነግሯል። በዚህም መሰረት የፌደሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ባደረጉት ስብሰባ ውድድሩ ከመስከረም 26 – ጥቅምት 11 እንዲከናወን ወስነዋል። ነገር ግን አሁንም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊን ጨዋታ ጥቅምት 11 በአዲስ አበባ ስታዲየም አከናውናለው ብሎ መርሃ ግብር በማውጣቱ ፌደሬሽኑ መጠነኛ ለውጦች እንዲያደርግ ያስገድዱታል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህንን በተመለከተ ጥያቄ ያቀረብንላቸው የፌደሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ዮናስ ሃጎስ (ጋዜጠኛ) ምን አልባት በዛ ቀን የሚደረጉ መርሃ ግብሮች ላይ ወደ ፊት ማስተካከያ ሊደረግ እንደሚችል አስረድተዋል። ውድድሩ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ የሚካፈሉት ሶስቱ የአዲስ አበባ ክለቦች (መከላከያ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ) እንዲሁም ተጨማሪ የክልል ክለቦችን ጋብዞ እንደሚከናወን ተጠቁሟል። ከክልል ተጋባዥ ክለቦች መካከል ከአዳማ ከተማ ፣ ጅማ አባጂፋር ፣ ፋሲል ከነማ ፣ ወላይታ ድቻ እና ባህር ዳር ከተማ ጋር ንግግሮች እየተደረጉ እንደሆነ ነገር ግን የትኛውም ክለብ የተረጋገጠ ይፋዊ ምላሽ እንዳልሰጠ ተገልጿል።