ኢትዮጵያ በፊፋ የሃገራት ወርሃዊ ደረጃ ሁለት ስፍራዎችን አሻሽላለች

ዓለም አቀፉ የእግርኳስ ማህበር ፊፋ በየወሩ ይፋ በሚያደርገው የፊፋ ኮካ ኮላ የሃገራት የእግርኳስ ደረጃ በመስከረም ወር ኢትዮጵያ 1060 ነጥብ ይዛ 149ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ካለፈው ወር የሁለት ስፍራዎች መሻሻል አሳይታለች።

በነሃሴ እና ጳጉሜ ወራት በሀዋሳ ዓለምአቀፍ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎችን ያደረጉት ዋልያዎቹ በወዳጅነት ጨዋታ ከብሩንዲ ጋር 1-1 ሲለያዩ በ2019ኙ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ደግሞ ሴራሊዮንን አስተናግደው በጌታነህ ከበደ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ 1-0 ማሸነፍ ችለዋል። በወሩ ላሳዩት የደረጃ መሻሻልም በሁለቱ ጨዋታዎች ያስመዘገቡት ውጤት ምክንያት ሆኗል።

ፊፋ ከሰኔ ወር 2018 ጀምሮ በደረጃ አሰጣጡ ላይ ኤሎ (Elo Rating System) የተሰኘ አዲስ የነጥቦች ስሌት መጠቀም የጀመረ ሲሆን በዚህ ቀመር መሰረት ሃገራት በደረጃቸው መሻሻል እንዲችሉ በየወሩ ጨዋታ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

በዓለም የእግርኳስ ደረጃ አውሮፓዊቷ ቤልጂየም ቀዳሚውን ደረጃ ስትይዝ የዓለም ሻምፒዮኗ ፈረንሳይ በእኩል ነጥብ አንደኝነቱን በጋራ ተቆናጣለች። የደቡብ አሜሪካዋ ብራዚል ደግሞ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

በአፍሪካ ዋንጫ ዋንጫ ማጣርያ የኢትዮጵያ ምድብ ውስጥ ከሚገኙት ሀገራት መካከል ጋና ካለፈው ወር ስድስት ደረጃዎችን ብትንሸራተትም 51ኛ ደረጃ በመያዝ ከምድባችን ቀዳሚ ነች። አምስት ደረጃዎችን ያሻሻለችው ኬንያ 107ኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ በኢትዮጵያ የ1-0 ሽንፈት ያስተናገደችው ሴራሊዮን ሶስት ደረጃዎችን አሽቆልቁላ 114ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ባሀማስ እና ቱርክስ ኤንድ ካይኮስ ደሴቶን የመጨረሻውን (210ኛ) ደረጃን የያዙ ሀገራት ናቸው።