ጅማ አባ ጅፋር የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቀቀ

የፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮኑ ጅማ አባጅፋር ዐወት ገብረሚካኤል እና ከድር ሳሊህን ሲያስፈርም ዲዲዬ ለብሪን በቀጣዮቹ ቀናት እንደሚያስፈርም ይጠበቃል። 

ዐወት ገ/ሚካኤል ከ2004 ጀምሮ ከተጫወተበት አሳዳጊ ክለቡ ኤሌክትሪክ ጋር የነበረውን የአንድ ዓመት ኮንትራት የውል ማፍረሻ በመክፈል መልቀቂያውን የወሰደ ሲሆን የምዕራብ ኢትዮጵያውን ክለበ በአንድ ዓመት ውል ተቀላቅሏል። ባህር ዳር ከተማን ለመቀላቀል ተቃርቦ የነበረው የቀኝ መስመር ተከላካዩ ዐወት በጅማ አምና መልካም ጊዜ ያሳለፈውና ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያመራው ኄኖክ አዱኛን ክፍተት እንደሚሸፍን ታምኖበታል።

ከድር ሳሊህ ሌላው የጅማ አባ ጅፋር ፈራሚ ነው። የመስመር አጥቂው አምና በወልዋሎ እንደክለቡ ሁሉ ድንቅ አጀማመር ቢያደርግም ቀስ በቀስ ተቀዛቅዞ ታይቷል። ከወልዋሎ ጋር የአንድ ዓመት ውል የነበረው የቀድሞው የአውስኮድ አጥቂ  በውሉ ዙርያ ከወልዋሎ ጋር የነበረውን አለመግባባት መፍታቱን ተከትሎ ወደ ጅማ አባጅፋር በአንድ ዓመት ውል አምርቷል።

ክለቡ በቀጣይ ቀናት በይፋ እንደሚያስፈርመው የሚጠበቀው አይቮሪኮስታዊው ዲዲዬ ለብሪ ነው። የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቹ እንደ ዐወት ሁሉ ቀሪ የአንድ ዓመት ውል ቢኖረውም ለኤሌክትሪክ የውል ማፍረሻ ለመክፈል ከስምምነት በመደረሱ ወደ ሀገር ቤት እንደመጣ የጅማ አባ ጅፋር ተጫዋች መሆኑ ይረጋገጣል።

(ፎቶ ማስተካከያ – ከላይ በቀኝ በኩል የነበረው ፎቶ የከድር ሳይሆን የሌላ ተጫዋች የነበረ ሲሆን በኤዲት ተስተካክሏል)