ሴቶች ዝውውር | ጥረት ሁለት ተጨዋቾችን ሲያስፈርም የሁለት ተጨዋቾችን ውል አድሷል

አምና በ14 ክለቦች መካከል ሲካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ዲቪዝዮን ውድድርን በበላይነት በማጠናቀቅ ወደ ኢትዮጵያ አንደኛ ዲቪዚዮን እርከን ያደገው ጥረት ኮርፖሬት ዘግየት ብሎ ወደ ዝውውር ገበያው በመግባት ሲሆን ሁለት  አዳዲስ ተጨዋቾችን ወደ ክለቡ ቀላቅሏል። 

በ2009 የውድድር ዓመት ቡድኑን ካፈረሰው ዳሽን ቢራ ላይ የሴቶች ቡድኑን ሙሉ ለሙሉ በመረከብ ውድድር እያደረገ የሚገኘው ጥረት ኮርፖሬት አምና በ2ኛ ዲቪዚዮኑ ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ መቅረብ መቻሉ የታየ ሲሆን በቀጣይ በፕሪምየር ሊግ ላይ ውጤት ለማምጣት እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። በዚህም መሰረት ክለቡ በቅድሚያ የአሰልጣኝ ሰርካዲስ እውነቱን ውል ለአንድ ዓመት ካራዘመ እና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ካስተካከለ በኋላ ወደ ዝውውር ገበያው ፊቱን አዙሯል።

የመጀመሪያዋ የክለቡ ፈራሚ አዲስ ንጉሴ (ፎቶ ከላይ) ስትሆን በ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ያሳየችውን ተስፋ ሰጪ ብቃት ተከትሎ ሀዋሳ ከተማን ለቃ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ተቀላቅላ የነበረ ሲሆን በጉዳት የታጀቡ ሁለት የውድድር ዓመታትን አሳልፋለች። እንደ አዲስ ሁሉ በልደታ ክፍለ ከተማ በተከላካይ አማካይ ስፍራ የምትጫወተው መሰረት ገ/እግዚአብሄር በተመሳሳይ በአንድ ዓመት ውል ወደ ክለቡ መቀላቀሏ ተገልጿል።

አሳቤ ሙሶ

ጥረት ከአዲሶቹ ተጨዋቾች ውጪ የነባር ተጨዋቾችንም ውል እያደሰ ይገኛል። አሳቤ ሙሶ እና ሊዲያ ጌትነትም በአንድ አመት ውላቸውን ማደሳቸው ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በተያያዘ ዜና ክለቡ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን መቀመጫውን ባደረገበት ባህር ዳር ከተማ ከመስከረም 22 ጀምሮ ለማከናወን የመቀደ ሲሆን ተጨማሪ አዳዲስ ተጨዋቾችን ከዝግጅቱ መጀመር በፊት ለማምጣት እንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ ተነግሯል።