ኢትዮጵያ ዋንጫ | መከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ለፍፃሜ አልፈዋል

በኢትዮጵያ ዋንጫ ዛሬ ለፍፃሜ ለማለፍ  በተደረገ ጨዋታ መከላከያ ኢትዮጵያ ቡናን 1-0 በመርታት ለተከታታይ አራተኛ ጊዜ ለፍፃሜ መቅረብ ችሏል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ከውድድሩ ራሱን ያገለለው ጅማ አባ ጅፋርን በፎርፌ በማሸነፍ ነው ወደ ፍፃሜው የተሸጋገረው።

ቀን 8:00 ሰዓት ሲል በሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም መከላከያን ከኢትዮጵያ ቡና ያገናኘው ጨዋታ በመከላከያ አሸናፊነት ተደምድሟል። ሁለቱም ክለቦች በአመዛኙ በነባር ተጨዋቾቻቸው ወደ ሜዳ ቢገቡም አዳዲስ ተጫዋቾቻቸውንም ተጠቅመዋል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል አዲስ ፈራሚው ግብ ጠባቂ ኢስማኤል ዋቴንጋ፣ ጋናዊው ካሉሻ አልሀሰን እና የቀኝ መስመር ተመላላሹ ተካልኝ ደጀኔ በቋሚነት የተሰለፉ ሲሆን መከላከያ በአንፃሩ አበበ ጥላሁን ፣ ተመስገን ገ/ኪዳን ፣ ዓለምነህ ግርማን እና ዳግም ክለቡን የተቀላቀለው ፍሬው ሰለሞንን ተጠቅሟል።

በርከት ባሉ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በታጀበው እና ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በብቃት በመሩበት ይህ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ አድርገዋል። መከላከያ በመልሶ ማጥቃት በቀኝ መስመር በፍሬው ሰለሞን በኩል አመዝኖ ሲጫወት ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ በአህመድ ረሺድ ሰብሮ ለመግባት በሚደረግ ጥረት እና በሚኪያስ መኮንን ግላዊ እንቅስቃሴ ታግዞ በመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መልኩ መንቀሳቀስ ችሏል። ከዚህ በተጨማሪ ጨዋታው የኃይል አጨዋወቶችን ያስተናገደም በመሆኑ በርከት ያሉ ቢጫ ካርዶችም ተመዘውበታል ።

የመጀመሪያ የግብ አጋጣሚን በመፍጠሩ ረገድ ቡና ቀዳሚው ነበር። 15ኛው ደቂቃ ላይ ካሉሻ አልሀሰን በድንቅ ብቃት ወደ ሳጥን ጠርዝ ገብቶ ለአማኑኤል ዮሀንስ የሰጠውን ኳስ አማኑኤል በቀጥታ ቢመታም ይድነቃቸው ኪዳኔ አድኖበታል። ከግብ ሙከራዎች ይልቅ በግል የሚንቀሳቀሱ ተጫዋቾች መብዛታቸው ደግሞ የጠራ የግብ እድሎችን በተደጋጋሚ ለመመልከት ያልቻልንበት ዋነኛው ምክንያት ነበር። ይሁን እንጂ መከላከያም በአዲስ ፈራሚው ተመስገን ገ/ኪዳን እና በምንይሉ ወንድሙ ከዳዊት እስጢፋኖስ እና ቴዎድሮስ ታፈሰ የሚነሱ አጋጣሚዎችን ለመጠቀም ቢሞክርም ኃይል ተቀላቀለበት አጨዋወት ሲከተሉ የነበሩት ቶማስ ስሞረቱ እና በአማካይ ተከላካይነት የተሰለፈው ክሪዝስቶም ንታንቢ ፈተና ሆነውባቸዋል። በተለይም ምንይሉ  ያገኛቸውን ዕድሎች በቀላሉ ሲያመክን ተመልክተናል። ቡናዎች በመጨረሻዎቹ የመጀመሪያው አጋማሽ ደቂቃዎች በአስራት ቱንጆ እና አህመድ ረሺድ ዕድሎችን ቢያገኙም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ ተሻሽለው ወደ ሜዳ የገቡት መከላከያዎች መሻሻለቸው በውጤት ሲታጀብ በፊት መስመር ላይ ከአስራት ቱንጆ በቀር ሁነኛ አጥቂ ያጣው ኢትዮጵያ ቡና ግን ዋጋ ለመክፈል ተገዷል። ከመልበሻ ቤት ገና እንደገቡ ሚኪያስ መኮንን ለአማኑኤል ዮሀንስ የሰጠውን ኳስ አማኑኤል ከርቀት አክርሮ መቶ ለጥቂት በግቡ ግርጌ ወጥታበታለች። ከዚህች አጋጣሚ በኋላ በቅፅበት በመልሶ ማጥቃት ወደ ኢትዮጵያ ቡና የግብ ክልል መድረስ የቻሉት መከላከያዎች ወሳኟን ግብ አግኝተዋል። በአጋጣሚው በ48ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው የግራ መስመር ተከላካይ ተካልኝ ደጀኔ ምንይሉ ወንድሙ ላይ በግብ ክልል ውስጥ ጥፋት በመስራቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ምንይሉ ወንድሙ ወደ ግብነት ቀይሮታል። ከግቧ በኃላ አሁንም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጫና የፈጠሩት መከላከያዎች ነበሩ። ፍሬው ሰለሞን ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ ምንይሉ ወንድሙ እና ተቀይሮ የገባው ዳዊት ማሞ የሚያደርጉት ቅብብል እና ወደ ግብ ክልል ለመግባት የሚያደርጉት ጥረትም አስገራሚ ነበር። ይሁንና ጨዋታው ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት በመከላከያ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። መከላከያም ለአራተኛ ተከታታይ አመት ለፍፃሜ ሲደርስ ኢትዮጵያ ቡና ከአስር ዓመታት በኋላም የውድድሩ ታሪኩን መቀየር ሳይችል ቀርቷል።

10:00 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ጅማ አባ ጅፋር ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋሮች በውድድሩ ላይ አንሳተፍም በማለታቸው እና በሜዳ ላይም ባለመገኘታቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀጥታ የፎርፌ አሸናፊ ሆኖ ለፍፃሜ ማለፍ ችሏል። ይህን ጨዋታ ለመምራት የተመደቡት ዋና ዳኛ በላይ ታደሰ እና ረዳቶቻቸው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾችን ወደ ሜዳ ካስገቡ እና ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ከሜዳ ወጥተዋል።

ህዳር ወር ላይ የጀመረው የ2010 የኢትዮጵያ ዋንጫ በመጪው ቅዳሜ መስከረም 19 ቀን 2011 ሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታድየም ላይ ሲጠናቀቅ ሁለቱ የውድድሩ ውጤታማ ክለቦች የሆኑት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ ዋንጫውን ለማንሳት እና የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ትኬታቸውን ለመቁረጥ ይፋለማሉ።