የ2010 ኢትዮጵያ ዋንጫ ፍፃሜ – ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መከላከያ

ከ2010 የውድድር ዓመት ተላልፎ ወደ 2011 የተሻገረው የኢትዮጵያ ዋንጫ ነገ መከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በሚገናኙበት ጨዋታ ይፈፀማል።

በፕሪምየር ሊጉ ክለቦች መካከል ካለፈው ዓመት ሚያዚያ 12 ጀምሮ አለፍ አለፍ እያለ ሲከናውን የቆየው የኢትዮጵያ ዋንጫ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል። አንድ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ብቻ የተስተናገደበት ውድድሩ መከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስን ነው በፍፃሜው የሚያፋልመው። ባሳለፍነው ማክሰኞ በሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታድከም ኢትዮጵያ ቡናን በምንይሉ ወንድሙ ብቸኛ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ መርታት የቻለው መከላከያ ለአራተኛ ተከታታይ ጊዜ የፍፃሜ ተካፋይ መሆን ሲችል ጅማ አባ ጅፋርን በፎርፌ ያለፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በፕሪምየር ሊጉ ያመለጠውን የአፍሪካ መድረክ ተሳትፎ መልሶ ለማግኘት የሚፋለም ይሆናል።

መከላከያ ለፍፃሜው መድረሱን ካረጋገጠበት የኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ አስቀድሞ ሁለት የሊጉን ክለቦች ከውድድሩ አስወጥቷል። በሰኔ ወር አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማን 3-2 በማሸነፍ ውድድሩን የጀመረው ክለቡ ሐምሌ ላይ ደግሞ በሩብ ፍፃሜው ፋሲል ከተማን 1-0 በመርታት ነበር ወደ ግማሽ ፍፃሜው ማለፍ የቻለው። ቅዱስ ጊዮርጊስም ከመከላከያ ጋር በተመሳሳይ ዕለት ውድድሩን ሲጀምር ያለፈውን የውድድሩ ሻምፒዮን ወላይታ ድቻን 1-0 በመርታት ነበር። ፈረሰኞቹ ቀጣዩ ተጋጣሚያቸው ሲዳማ ቡናን በፍፁም ቅጣት ምት 7-6 አሸንፈውም የፎርፌ ውጤት ላገኙበት የአባ ጅፋሩ ጨዋታ ደርሰዋል።

በዚህ ውድድር ላይ በቅርብ ዓመታት መልካም ውጤት እያስመዘገበ የመጣው መከካከያ (አራት ተከታታይ ፍጻሜዎች) አምና በወላይታ ድቻ የተነጠቀውን ክብር መልሶ ለማግኘት የነገውን ጨዋታ እየጠበቀ ይገኛል። ክለቡን ባሳለፍነው የውድድር ዓመት የተረከቡት አሰልጣኝ ሥዩም ከበደም ስለውድድሩ እና ስላነገው ፍፃሜ በተለይም ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ” ጥሎ ማለፋ ከ2010 መተላለፋ ይታወቃል። ዝግጅታችንን እያደረግን ያለነው በ2011 ላይ ባለው ውድድር ላይ ጥሩ ተፎካካሪ ለመሆን ነው። የ2010 ጥሎ ማለፍ በማሸነፍ በአፍሪካ ጨዋታ ላይ መሳተፍ ፍላጎት አለን ፤ ጉዛችንም ጥሩ ይመስለኛል። ለነገው ጨዋታ ላይ የተለየ ዝግጅት አላደረግንም። ቡድናችን ኢትዮጵያ ቡናን አሸነፎ እንደምምጣቱ በተጨዋቾችም ሆነ በኔ በኩል ጥሩ መነቃቃት ላይ ነን ፤ ወደ ሜዳም የምንገባው ለማሸነፍ ነው። ” ብለዋል።

በሊጉ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር እስከመጨረሻው ሳምንት ድረስ አንገት ለአንገት ተናንቆ በመጨረሻም ዋንጫውን ያጣው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ላይ የመሳተፍ ዕድሉንም ነበር አብሮ ያጣው። ሆኖም በኢትዮጵያ ዋንጫ እስከ ፍፃሜው ድረስ መምጣቱ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ የመሳተፍ ሌላ አጋጣሚን ፈጥሮለታል። የፈረሰኞቹ ምክትል አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ለሶከር ኢትዮጵያ ጋር በሰጡት አስተያየት ለጨዋታስ በሚገባ ዝግጀት እንዳደረጉ ገለፀዋልጰ ” ለጨዋታው ጥሩ ዝግጅት አድርገናል ፤ ለብሔራዊ ቡድን ተመርጠው የነበሩት ተጨዋቾቻችንም ከታመለሱ በኋላ ዝግጅታችንን አጠናክረን ቀጥለናል። አዳዲስ ፈራሚዎቻችንም ከቡድኑ ጋር በሚገባ እየተዋሀዱ ይገኛሉ። የሊጉን ዋንጫ በማጣታችንም ይህንን ዋንጫ በደንብ እንፈልገዋለን። ይህን ዕድል ተጠቅመን ጨዋታውን በማሸነፍም በአህጉራዊ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ ሆነናል። በመጨረሻው ልምምዳችን ተጨዋቾቻችን በጥሩ ጤንነት እና የአዕምሮ ደረጃ በላይ አንደሚገኙ ተመልክተናል።” በማለት ስለፍፃሜው አስተያየት ሰጥተዋል።

የሁለቱ ክለቦች የፍፃሜ ፍልሚያ ነገ በ09:00 ሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታድየም ላይ የሚደረግ ሲሆን አሸናፊው ቡድን በ2019 የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ የሚሳተፍ ይሆናል።