ድህረ ጨዋታ አስተያየት – ሥዩም ከበደ (መከላከያ)

የ2010 የውድድር ዓመት የኢትዮጵያ ዋንጫ በዛሬው ዕለት ፍፃሜውን ሲያገኝ መከላከያ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመለያ ምቶች 3-2 በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል። ባለፈው የውድድር ዓመት አጋማሽ ክለቡን በአሰልጣኝነት የተረከቡት ሥዩም ከበደም ከክለቡ ጋር የመጀመርያ ዋንጫቸውን አንስተዋል። 

አሰልጣኝ ሥዩም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ለጋዜጠኞች የሰጡትን አሰለያየት እንዲህ አቅርበነዋል:-

ስለ ውድድሩ

ከነሐሴ 10 ጀምሮ ስንዘጋጅ የነበረው ለዚ ውድድር በማሰብ ነው። ምክንያቱም ይህ ትልቅ ውድድር ነው። ኢንተርናሽናል ውድድርን አስበን ነበር ዝግጅት ስንሰራ የቆየነው። ስለዚህ በስራነው ስራ ልክ ድሉ ይገባናል።

ስለ ጨዋታው 

በመጀመሪያው አጋማሽ ከኋላ እስከ መሀል የነበረው እንቅስቃሴ ጥሩ ነበር፤ ፊት ላይ ትንሽ ይቀረን ነበር። ከዕረፍት መልስ ግን ያለብንን ችግር በመቅረፍ ጥሩ ተንቀሳቅሰናል። ጨዋታውን በ90 ደቂቃ ውስጥ መጨረስ የሚያስችሉ እድሎች ፈጥረን ነበር፤ ፈጣሪ ይመስገን የምንፈልገውን አግኝተናል።

የኢትዮጵያ ዋንጫ ስኬትን በሊግ ላይ ስለመድገም 

የሊጉ ውድድር ላይ ትልቅ ጫና አለ። በአጥቂ በኩል በፍቃድ ላይ ያለው ፍፁም ገብረማርያም ሲመለስ ያለብንን ችግር እየቀረፍን እንመጣለን። በሲቲ ካፕ ውድድር ላይም ራሳችንን በደንብ እንፈትሻለን። በሊጉ የተሻሉ አጥቂ ስብስብ ያለው በአሁኑ ሳዓት መከላከያ ነው። ወደ ቡድኔ ከመጡት አዳዲስ 7 ተጨዋቾች መካከል በ6ቱ ተሳክቶልናል። ምክንያቱም ተጫዋቾቹ የመጡት ባለቡን ክፍት ቦታዎች ነው። ከአሰልጣኝ እስከ ተጫዋች በ2011 ታሪክ ለመስራት ትልቅ ተነሳሽነት ላይ በመሆናችን ሁላችንም ኃላፊነታችንን እንወጣለን። የኋላውን ታሪክ ጥለን በ2011 መከላከያ ለሻምፒዮንነት ነው የሚጫወተው።