የዳኞች ስልጠና ዛሬ ተጀምሯል

ለቀጣይ አምስት ቀናት የሚዘልቅ የዳኞች ስልጠና በዛሬው ዕለት በጁፒተር ሆቴል ተጀምሯል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማህበር /ፊፋ/ ጋር በተመተባበር ያዘጋጀው ስልጠና የመክፈቻ ፕሮግራም ዛሬ ተካሂዷል። ለ35 ኢንተርናሽናል እና ኤሊት ፌደራል ዳኞች የተዘጋጀው የከፍተኛ የእግር ኳስ ዳኞች የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና /FIFA MA ELITE REFEREE’S COURSE/ ዛሬ ከ9 ሰዓት ጅምሮ አሰልጣኞች ፣ ሰልጣኞች እና የክብር እንግዶች በተገኙበት በጁፒተር ሆቴል ነበር በመክፈቻ ስነ-ስርዓት የተከፈተው።

ፊፋ እና ካፍ ያሁኑን እና የከዚህ ቀደሞቹን ስልጠናዎች ወደ ሀገራችን እንዲመጡ በማስቻሉ ምስጋናቸውን ያቀረቡት የፌዴሬሽኑ የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ በመክፈቻው ስነስርዓት መግቢያ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢንተርናሽናል ዳኞቻችን እያሳዩ ያሉት አቋም መልካምነት ሌሎች ተጨማሪ በተለይም ሴት አርቢትሮቻችን በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ውድድሮችን የመምራት ዕድል እንዲያገኙ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል። አቶ ዮሴፍ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዳኞች ኮሚቴም የዳኞቻችን ብቃት ይበልጥ እንዲሻሻል ለማድረግ መሰል ስልጠናዎችን ለማዘጋጀት ጥረቱን እንደሚቀጥል በመግለፅ ስልጠናውን በይፋ አስጀምረዋል። ስልጠናው ከዛሬ ጀምሮ እስከ መስከረም 23 የሚቀጥል ይሆናል።