አዳማ ከተማ ሁለት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሀምን ዋና አሰልጣኝ የቀጠረው አዳማ ከተማ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ስመ ጥር ከሆኑ ተጫዋቾች ይልቅ አዳዲስ ፊቶችን ወደ ክለቡ ከከፍተኛ ሊግ ማምጣቱን ቀጥሎበታል። በዚህም ዱላ ሙላቱ እና አዲስዓለም ደሳለኝን ወደ ቡድኑ በሁለት ዓመት ውል ቀላቅሏል፡፡ 

የመስመር ተጫዋቹ ዱላ ሙላቱ በነቀምት ከተማ የእግር ኳስ ህይወቱን ከጀመረ በኃላ ሀዲያ ሆሳዕናን በ2007 ተቀላቅሎ ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ተጫዋቾች ነበር። ዱላ 2010 ላይ ሀዲያ ሆሳዕናን ለቆ ወደ መቐለ ከተማ በአንድ ዓመት ውል ቢያመራም በተፈለገው ልክ በቡድኑ ውስጥ ስኬታማ ጊዜን ባለማሳለፉ በመጋቢት ወር ቀሪ ኮንትራት እየቀረው ወደ ቀድሞ አሰልጣኙ ግርማ ታደሰ ቡድን ደቡብ ፖሊስ በማምራት አጭር ቆይታን አድርጓል።

አዲስዓለም ደሳለኝ በድጋሚ አዳማን የተቀላቀለ ተጫዋች ሆኗል። በአዳማ ከተማ የእግር ኳስን ህይወቱን የጀመረው ተጫዋቹ በሙገር ሲሚንቶ እንዲሁም በሲዳማ ቡና እንዲሁም ያለፉትን ሁለት ዓመታት በሰበታ ከተማ ከተጫወተ በኋላ ወደ ቀድሞ ክለቡ ተመልሷል።

ከአዳዲስ ተጫዋቾች ጎን ለጎን የነባር ተጫዋቾቹኝ ውል እያደሰ የሚገኘው አዳማ ከተማ የአይቮሪኮስታዊው አማካይ ኢስማኤል ሳንጋሬን ውል በአንድ ዓመት አራዝሟል፡፡

ከሁለቱ ተጫዋቾች ቀደም ብሎ አዳማ ከተማ ዐመለ ሚልኪያስ፣ ሀብታሙ ሸዋለም፣ ሙሉቀን ታሪኩ፣ ኄኖክ ካሳሁን፣ አብይ ቡልቲ፣ ቴዎድሮስ በቀለን ማስፈረሙ የሚታወስ ነው።

*በቅድሚያ ተፅፎ በነበረው ዘገባ ላይ ሱራፌል ጌታቸው ለአዳማ ከተማ ፈረመ የሚለው በስህተት የተካተተ መሆኑን ከይቅርታ ጋር እንገልፃለን።