ድሬዳዋ ከተማ ሁለት ተጨዋቾችን አስፈርሟል

የምስራቁ ክለብ የአጥቂ አማራጮቹን ያሰፋባቸውን ዝውውሮች አጠናቋል።

አምና ከመውረድ ለጥቂት የተረፈው ድሬዳዋ ከተማ ዘንድሮም ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ላለመገኘት ራሱን በዝውውሮች እያጠናከረ ነው። አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌን ከሾመ በኃላ ስምንት አዳዲስ ተጨዋቾችን ያመጣው ድሬዳዋ አሁን ደግሞ የፊት መስመሩ ላይ ትኩረት በማድረግ ተጨማሪ ተጨዋቾችን በጁ አስገብቷል።

ከአዳዲሶቹ ፈራሚዎች መካከል ኃይሌ እሸቱ አንዱ ነው። ከሞጆ የተገኘው ኃይሌ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካደገ በኋላ ክለቡ በዛው ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊግ ቢወርድም በግሉ መልካም ጊዜን ማሳለፍ ችሎ ነበር። የፊት አጥቂው ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ደግሞ በተመሳሳይ የመውረድ ዕጣ በገጠመው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ውስጥ አሳልፏል። ዓመቱን በጉዳት የጀመረው ኃይሌ ከቡድኑ ጋር ቀስ በቀስ መዋኃድም ችሎ ነበር። ኃይሌ የአንድ ዓመት ውሉን በስምምነት አፍርሶ ነው ወደ ድሬዳዋ ያመራው።

ሌላው ብርቱካናማዎቹን የተቀላቀለው አጥቂ ናሚቢያዊው የ25 ዓመት ተጨዋች ኢታሙኑዋ ኬይሙይኔ ነው። በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ናሚቢያዊ ተጨዋች የሚሆነው ኬይሙይኔ በሀገሩ ሊግ ለቱራ ማጂክ ሲጫወት የቆየ ሲሆን ሞሮኮ ባዘጋጀችው 2018ቱ የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) ላይ መሳተፍ ችሎ ነበር። ድሬዳዋ ከተማ አምና ተደጋጋሚ የተጨዋቾች ለውጥ ሲያደርግበት በነበረው የፊት መስመሩ ላይ ከሀብታሙ ወልዴ እና ዳኛቸው በቀለ በተጨማሪ ሁለቱን አዳዲስ ፈራሚዎች ማግኘቱ በቦታው ላይ ያለውን አማራጭ እንደሚያሰፋለት ይታመናል።