ደደቢት ሙሉ ለሙሉ ወደ መቐለ አምርቷል

ደደቢት እግርኳስ ክለብ ከወራት በፊት መቀመጫ ከተማው፣ የዝውውር አካሄዱ እና የደሞዝ ጣርያው ላይ ለውጥ እንዳደረገ ማስታወቁን ተከትሎ ከትላንት በስቲያ ማምሻውን ጠቅልሎ ወደ መቐለ አምርቷል። 

ከተመሰረተበት 1989 ጀምሮ እንዲሁም ወደ ለክነብት ከተቀየረበት 1990ዎቹ አጋማሽ ወዲሀ በአዲስ አበባ የውስጥ ውድድሮች፣ በብሔራዊ ሊግ እና ፕሪምየር ሊግ ያደረጋቸውን የሜዳው ጨዋታዎችን መቀመጫው ባደረገበት አዲስ አበባ ሲያደርግ የቆየው ደደቢት መቀመጫውን ወደ መቐለ ከተማ ለማዞር እንቅስቃሴ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን 30 ተጫዋቾቹን እና 3 የአሰልጣኝ ቡድኑን አባላት በመያዝ ጠቅልሎ ቅዳሜ ምሽት 2:00 ላይ ወደ መቐለ ሲገባ በክለቡ አመራሮች አቀባበል ተደርጎለታል።

ደደቢት በአርሴማ ሆቴል ተቀምጦ የ2011 የውድድር ዓመት ዝግጅቱን የሚያደርግ ሲሆን በዛሬው ዕለት ማለዳ የመጀመርያውን ልምምድ በመቐለ አከናውኗል። ቡድኑ ቢያንስ ለቀጣዩ አንድ ወር በሆቴል እንደሚቆይ ሲገለፅ ቀጣይ ሁኔታው ወደፊት ይገለፃልም ተብሏል። (ደደቢት ከ2008 ጀምሮ የዋናው ቡድን ተጫዋቾችን በካምፕ የማኖር አሰራር ማስቀረቱ የሚታወስ ነው።)