ዋልያዎቹ ዛሬ አመሻሽ ቀለል ያለ ልምምድ ባህር ዳር ላይ ሰርተዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ2019ኙ የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በምድብ 5 ከኬንያ፣ ጋና እና ሴራሊዮን ጋር ተደልድሎ የምድብ ጨዋታውን እያከናወነ ይገኛል። ባህር ዳር ላይ ከኬንያ ጋር ለሚያደርገው የምድቡ ሶስተኛ ጨዋታም ከዛሬ ጀምሮ ልምምድ ማከናወን ጀምሯል።

ቡድኑ ዛሬ ረፋድ ስለ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በአምበሉ እና አሰልጣኙ አማካኝነት መግለጫ ከሰጠ በኋላ በቀጥታ ጨዋታው ወደሚደረግበት ባህር ዳር ያቀና ሲሆን ልምምዱንም ዛሬ ጀምሯል። ብሔራዊ ቡድኑ ከ45 ደቂቃዎች የዓየር ላይ ጉዞ በኋላ ባህር ዳር እንደደረሰ በከተማው ነዋሪ እና የስፖርት ቤተሰብ ደማቅ አቀባበል የተደረገለት ሲሆን ከአቀባበሉ በኋላም በማረፊያነት ወደመረጠው ብሉ ናይል ሆቴል አቅንቷል። 

የቡድኑ ተጨዋቾች መጠነኛ እረፍት ካደረጉ በኋላም ከ11:30 ጀምሮ የሪከቨሪ ልምምዶችን ባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም አጠገብ በሚገኘው የልምምድ ሜዳ አከናውነዋል። በልምምዱ ከፋሲል ከነማ የተመረጡት ሶስቱ ተጨዋቾች (ሙጂብ ቃሲም፣ ሽመክት ጉግሳ እና አምሳሉ ጥላሁን) እንዳልተገኙ የተሰማ ሲሆን ከነገ ጀምሮ ቡድኑን ተቀላቅለው መደበኛ ልምምዳቸውን እንደሚሰሩ ለማወቅ ተችሏል። የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ (ኢንስትራክተር) ከቡድኑ ጋር ወደ ባህር ዳር ከማቅናታቸው በፊት በሰጡት አስተያየት የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ ሳላዲን በርጌቾ፣ አስቻለው ታመነ እና በኃይሉ አሰፋ ከጉዳት እና ከጨዋታ መደራረቦች ጋር በተያያዘ ከቡድኑ ጋር አብረው እንደማይጓዙ በተናገሩት መሰረት ሶስቱም በልምምዱ ያልተገኘ ሲሆን ነገ ምሽት 11 ሰዓት በሚወጣ የኤም አር አይ ውጤት መሰረት ቀጣይ ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር ያላቸው እጣ ፈንታቸው እንደሚወሰን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታው እስከሚደረግበት ዕለት (ረቡዕ መስከረም 30) መደበኛ ሰባት ልምምዶችን እንደሚሰራ ሲጠበቅ ከፊታችን ሀሙስ ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ድረስ በውጪ ሀገራት የሚጫወቱ አራቱ ተጨዋቾች (ሽመልስ፣ ቢኒያም፣ ጋቶች እና ዑመድ) በማካተት በሙሉ ስብስቡ ልምምዱን እንደሚቀጥል ተነግሯል።