የ2011 የከፍተኛ ሊግ ውድድር ህዳር 16 ይጀምራል

የ2011 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ህዳር 16 እንደሚጀመር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለሶከር ኢትዮጵያ አስታውቋል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚያድጉትን ሶስት ክለቦች የሚለየው የ2011 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ  ውድድር በ32 ክለቦች መካከል በየዓመቱ የሚደረግ ሲሆን ዘንድሮም ካለፉት ዓመታት በተመሳሳይ በሁለት ምድቦች ተከፍሎ እንደሚደረግ የተገለፀ ሲሆን የዕጣ ማውጣት ስነ ስርዓቱ ውድድሩ ከመጀመሩ አንድ ወር ቀደም ብሎ ጥቅምት 15 እንደሚከናወን ተነግሯል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ደቡብ ፖሊስ ባህር ዳር ከተማ እና ሽረ እንዳሥላሴ ከዚህ ውድድር ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደጉ ሲሆን ከሊጉ የወረዱት አርባምንጭ ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወልዲያ ይተኳቸዋል። ከአንደኛ ሊግ ያደጉት አቃቂ ቃሊቲ፣ ገላን ከተማ፣ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ፣ ሺንሺቾ፣ ሶዶ ከተማ፣ አርሲ ነጌሌ ሲሆኑ ከከፍተኛ ሊጉ በወረዱት ፌዴራል ፖሊስ፣ ወሎ ኮምቦልቻ፣ ሱሉልታ ከተማ፣ መቂ ከተማ፣ ድሬዳዋ ፖሊስ እና ሻሸመኔ ከተማ ምትክ የሚሳተፉ ይሆናል።