የሴቶች ዝውውር | ኢትዮ ኤሌክትሪክ 14 ተጨዋቾችን አስፈርሟል

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ11 ነባር እና በ14 አዳዲስ ተጨዋቾች ቡድኑን አዋቅሯል

እንደ ዋናው የወንዶች ቡድኑ ሁሉ በሴቶቹም ቡድኑ ወደ ሁለተኛው የሊግ ዕርከን የመውረድ ዕጣ የገጠመው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዳግም የመመለስ ጥረቱን ለማሳካት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በክለቡ ስር ባሉት ሁሉም ቡድኖች ውስጥ የአሰልጣኝ ለውጦችን በማድረግ በይፋ መሾሙም የጥረቱ የመጀመሪያው እርምጃ ነበር። በዚህም መሰረት አሰልጣኝ እየሩሳሌም ነጋሽ የሴቶቹን ቡድን የማሰልጠን ኃላፊነቷን መረከቧ ይታወሳል። ክለቡም የአሰልጣኝ ሹመቱን ከጨረሰ እና የሚቀጥሉ እንዲሁም አዲስ የሚቀላቀሉ ተጨዋቾችን ጉዳይ ከተጠናቀቀ በኋላ የሴቶች ቡድኑን ሙሉ ስብስብ  ከመስከረም 14 ቀን ጀምሮ ለቅድመ ውድድር ዝግጅት ወደ አዳማ ልኳል። 

አሰልጣኝ እየሩሳሌም ነጋሽ በመጪው የውድድር ዓመት በሁለተኛው የሴቶች የሊግ ዕርከን ይዛው ከምትቀርበው ቡድን ውስጥ አስራአንዱ ነባር ተጨዋቾች ናቸው። በዚህ ዝርዝር ውስጥ የሚካተቱ ደግሞ ዮርዳኖስ ፍሰሀ ፣ አትጠገብ ክፍሉ ፣ አለምነሽ ታመነ ፣ ዘይነባ ሰኢድ ፣ ትበይን መስፍን ፣ ጽዮን ፈየራ ፣ ቤተልሔም ከፍያለው ፣ አለምነስ ገረመው ፣ ሰናይት አስራት ፣ ማህደር ጋሻው እና አይናለም ጸጋዬ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከስምንት ክለቦች አስራ አራት ተጨዋቾችን ማስፈረም ችሏል። ከነዚህ ውስጥ የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ ሜሮን አብዱ ፣ ወርቅነሽ መልመላ ፣ ፍቅርተ አስማማው እና ሰሚራ ከማል (ፎቶ) ፤ የኢትዮጵያ ቡናዎቹ ቅድስት አባይነህ እና ገነት አንተነህ ፤ የደደቢቶቹ ብዙአየሁ አበራ እና መስታወት አራርሳ ፤ የልደታ ክ/ከተማዎቹ ለምለም ወልዱ እና ሀና ታደሰ ይገኙባቸዋል። በተጨማሪም ክለቡ ከአዲስ አበባ ከተማ እስራኤል ከተማን ፣ ከወጣቶች ስፖርት አካዳሚ መሳይ ተመስገንን ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አይናለም ወንድሙን እንዲሁም ሀና ቱርጋን ከመከላከያ ማስፈረሙ ታውቋል።