ከፍተኛ ሊግ | ደሴ ከተማ ተጨማሪ አምስት ተጫዋቾችን አስፈረመ

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ የሆነው ደሴ ከተማ ዘንድሮ በርከት ያሉ ተጨዋቾችን ወደ ቡድኑ እየቀላቀለ ሲሆን ትላንት ምሽት የአምስት ተጨዋቾችን ዝውውር አጠናቋል።

አምና በ30ኛ ሳምንት በተደረገው የፌደራል ፖሊስ እና ሽረ እንዳስላሴ ጨዋታ በተያዘ ክስ ደሴዎች ከሊጉ የመውረድ ስጋት አጭሮባቸው የፌደሬሽኑን የመጨረሻ ውሳኔ ሲጠባበቁ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን በሳምንቱ አጋማሽ ፌደሬሽኑ ክሱ ውድቅ መድረጉን በመግለፁ ስጋታቸውን ወደ ጎን በመተው ዳግም ወደ ዝውውር ገበያው ገብተዋል። 

በዚህም መሰረት ትላንት ክለቡ ሀቢብ ሀብታሙ ከአድዋ (ግብ ጠባቂ)፣ ማቲያስ መኮንን (ከሀዲያ ሆሳዕና አማካይ)፣ ግርማ ፅጌ (ከኢትዮጵያ መድን አማካኝ)፣ ጌድዮን ታደሰ (ከሰበታ ከተማ አጥቂ) እና አትክልት ንጉሴን (ከደቡብ ፖሊስ አጥቂ) ማስፈረሙ ለማወቅ ተችሏል። 

ትላንት ከፈረሙት አምስት ተጨዋቾች መካከል ሁለቱ (ጌዲዮን (ፎቶ) እና አትክልት) የአጥቂ መስመር ተጨቾች በመሆናቸው ክለቡ አምና ጨዋታዎችን የማሸነፍ ችግሩን ለመቅረፍ አስቦ ዝውውሩን እንዳደረገ ይገመታል። 

ክለቡ ከዚህ ቀደም የሰባት ተጨዋቾችን ዝውውር ማጠናቀቁን መግለፁ የሚታወስ ሲሆን ቡድኑ አምና ያሳየውን ደካማ እንቅስቃሴ ለማስተካከል እና በሊጉ ተፎካካሪ ለመሆን እስካሁን በድምሩ 12 ተጨዋቾችን ማስፈረም ሲችል የነባር ተጨዋቾችንም ውል እያራዘመ መሆኑን ክለቡ አስታውቋል።