የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የመጀመሪያ ቀን ውሎ

13ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ዛሬ በተደረጉ የምድብ አንድ ጨዋታዎች ሲጀምር ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ ቡና ድል ቀንቷቸዋል። 

መከላከያ 0-1 ኢትዮ ኤሌክትሪክ

(በሚካኤል ለገሠ)

ከውድድሩ ይፋዊ የመክፈቻ ጨዋታ (ኢትዮጵያ ቡና ከ አዳማ ከተማ) በፊት በተከናወነው የመከላከያ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ አምና ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወደ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የወረደው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የጨዋታ ብልጫ ወስዶ ሲንቀሳቀስ በተቃራኒው መከላከያዎች ደግሞ ተዳክመው ታይተዋል። ሁለት መልኮች በነበሩት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ መከላከያዎች የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል።

ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በመሩት ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ4-1-4-1 አስተላለፍ አዳዲስ እና ነባር ተጨዋቾችን በመቀላቀል ለጨዋታው ሲቀርቡ መከላከያዎች ደግሞ በ4-4-1-1 የተጨዋች አደራደር ቅርፅ ወደ ሜዳ ገብተዋል። በ9ኛው ደቂቃ ተመስገን ገ/ ኪዳን ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ አክርሮ በመታት ኳስ ጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ያስመለከተን ሲሆን ኳሷ ኢላማዋን ባለመጠበቋ የግቡን ቋሚ ታካ ወደ ውጪ ወጥታለች። በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ሙከራዎችን በማድረግ ጥሩ የነበሩት መከላከያዎች በ15ኛው ደቂቃ ላይም ከቅጣት ምት በተገኘች ዕድል በዳዊት እስጢፋኖስ ሌላ የግብ ማግባት አጋጣሚ አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ቀስ በቀስ ጨዋታውን መቆጣጠር የጀመሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ዳዊት ሙከራውን ካደረገ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚ አግኝተዋል። አቡበከር ደሳለኝ ከጦሩ ተከላካዮች ጀርባ በመሮጥ ያገኘውን ኳስ ለሃብታሙ ረጋሳ አመቻችቶለት ሀብታሙ ኳሷን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።


አሁንም ጫና ማሰደራቸውን የቀጠሉት ኤሌክትሪኮች የጥረታቸውን ፍሬ በ24ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። ሃብታሙ መንገሻ ከአቡበከር የደረሰውን ያለቀለት የግብ ማግባት ዕድል ግብ ጠባቂው አቤልን አታሎ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ከግቡ መቆጠር በኋላ የኤሌክትሪክ ተጨዋቾች የራስ መተማመናቸው ከፍ በማለቱ ኳሷን በአግባቡ ተቆጣጥረው የተጫወቱ ሲሆን ተደጋጋሚ የግብ ማግባት ሙከራዎችን ለመሰንዘር ግን ሲቸገሩ ታይቷል። ምንም እንኳን መከላከያዎች በዚህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተዳክመው ቢታዩም ከቆሙ ኳሶች ግን ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል። በዚሁ የጨዋታ እንቅስቃሴ በ36ኛው ደቂቃ ታፈሰ ሰርካ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ወደ ግብነት ለመቀየር የጣረ ሲሆን ኳሷ ኢላማዋን ባለመጠበቋ ወደ ውጪ ወጥታለች። ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ፍሬው ሰለሞን የኤሌክትሪኮች ግብ ጠባቂ ዮሃንስ የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ ግብ ሊያስቆጥር የሚችልበትን አጋጣሚ አግኝቶ አምክኗል።

በሁለተኛው አጋማሽ በርካታ ለውጦችን አድርገው ወደ ሜዳ የገቡት መከላከያዎች ተሽለው የተንቀሳቀሱ ሲሆን ወደ ግብ የመድረስ ችግር ግን ተስተውሎባቸዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ  ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወት ሲሞክሩ የነበሩት ኤሌክትሪኮች ኳሷን ከግብ ጠባቂያቸው ዩሃንስ ሲጀምሩ መከላከያዎች ምንም ጫና አለማድረጋቸው የጠቀማቸው ቢመስልም በሁለተኛው አጋማሽ ግን መከላከያዎች በመጠኑ ተጭነው በመጫወታቸው ሲቸገሩ ታይቷል።
ነገር ግን ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ በሁለተኛው ደቂቃ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሚኪያስ በየነ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ አክርሮ የመታት ኳስ የመሪነቱን ልዩነት ወደ ሁለት ከፍ ልታደርግ የምትችል የነበረች ቢሆንም ኳሷ ፊት ለፊት ስለነበረች አቤል በቀላሉ ተቆጣጥሯታል። ከዚህ ውጪ በ48ኛው ደቂቃ በመከላከያዎች በኩል ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አቅሌሲያ ግርማ በረጅሙ የተጣለለትን ኳስ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ የመታው ሲሆን ኳሳን ግብ ጠባቂው አምክኖበታል። በጥቅሉ ግን ሁለቱም ቡድኖች በሁለተኛው አጋማሽ አስቆጪ የግብ ማግባት አጋጣሚ ሳይፈጥሩ ጨዋታቸውን አጠናቀዋል። 


ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ የግራ መስመር ተከላካይ ቢኒያም ትዕዛዙ የጨዋታው ኮከብ በመሆን የተዘጋጀለትን ሽልማት ተረክቧል።
አዳማ ከተማ 2-3 ኢትዮጵያ ቡና

(በዮናታን ሙሉጌታ)

በኢትዮጵያ ቡና የኳስ ቁጥጥር የበላይነት በአዳማ ሜዳ ላይ አድልቶ የጀመረው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች ቀዝቀዝ ቢልም ቀጣዮቹ 10 ደቂቃዎች ግን በተቃራኒው ግለቱ ከፍ ብሎ የታየበት ነበር። በአዳማዎች በኩል 10ኛው ደቂቃ ላይ ቡልቻ ሹራ በግንባሩ ካደረገው ሙከራ አራት ደቂቃዎች በኋላ የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ዋቴንጋ ኢሳማ የሰራውን ስህተት ተከትሎ በረከት ደስታ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጥሯል። 


ሆኖም ኢትዮጵያ ቡናዎች በአንድ ደቂቃ ልዩነት ውስጥ ሉኩዋ ሱለይማን ሞክሮት ጃኮ ፔንዜ ካዳነው ኳስ በተገኘ ዕድል በቃልኪዳን ዘላለም አማካይነት አቻ ሆነዋል።  በግቧ የተነቃቁት ቡናዎች ጫና መፍጠራቸውን በመቀጠል 19ኛው ደቂቃ ላይ ያገኙት የማዕዘን ምት ተሻምቶ በአዳማ ተከላካዮች ከመራቁ በፊት በሉኩዋ ሱለይማን መሪ የሚሆኑበትን ግብ አግኝተዋል። 17ኛው ደቂቃ ላይም ዳንኤል ደምሴ በቀኝ በኩል በድንቅ ሁኔታ በመግባት ሰጥቶት ቃልኪዳን የሞከረው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ተጠቃሽ ነበር።  ቀጣዮቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች ግን ጨዋታው መልሶ የቀዘቀዘባቸው ነበሩ። ሆኖም የአዳማ ከተማ የ45ኛ ደቂቃ የቀኝ መስመር መልሶ ማጥቃት በቡልቻ ሹራ አቀባይነት እና በበረከት ደስታ ጨራሽነት ወደ ግብነት ተቀይሮ በ2-2 ውጤት ቡድኖቹ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ ከደቂቃዎች በኋላ ኢስማኤል ሳንጋር በአስገራሚ ፍጥነት ወደ ሳጥን ይዞ የገባውን ኳስ ኤፍሬም ዘካርያስ ሞክሮ ሲመለስበት ጨዋታው ተሟሙቆ የጀምሮ መስሎ ነበር። ሆኖን ግን አብዛኛዎቹ ደቂቃዎች በተለይም ሁለቱም ቡድኖች ኳስ መስርተው ለመጫወት ጥረት በሚያደርጉባቸው ጊዜያት ላይ መቀዛቀዝ የታየበት ነበር። ከዛ ይልቅ ወደ መልሶ ማጥቃት የቀረቡ አጋጣሚዎች በሁለቱም ቡድኖች በኩል ለሙከራዎች መፈጠር ምክንያት ሲሆኑ ይስተዋል ነበር። በአዳማ በኩል የቡልቻ ሹራ እና በረከት ደስታ ጥምረት በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ሲሆን ተቀይሮ የገባው የኢትዮጵያ ቡናው የመስመር አጥቂ ሚኪያስ መኮንንም የቡድኑን የቀኝ ክፍል እጅግ አስፈሪ አድርጎት ነበር። በተለይም 56ኛው ደቂቃ ላይ ሚኪያስ ከቀኝ መስመር ወደ ግራ የአዳማን ተከላካዮች በልዩ ቅልጥፍና እያታለለ ካለፈ በኋላ የሞከረው ኳስ ለጥቂት ነበር ወደ ውጪ የወጣው። በዚህ መልኩ አልፎ አልፎ ቡድኖቹ ወደ ግብ እየደረሱ ጨዋታው በአቻ ውጤት ለመጠናቀቅ በተቃረበበት ሰዓት 85ኛው አቂቃ ላይ በድጋሜ ከማዕዘን ምት የተሻገረው እና ጃኮ ፔንዜ በአግባቡ ያላወጣውን ኳስ ክሪዚስቶም ንታንቢ አስቆጥሮ ኢትዮጵያ ቡና ምድቡን ለመምራት ያስቻለውን ነጥብ ይዞ ወጥቷል።

ከወልዲያ ወደ ኢትዮጵያ ቡና የመጣው እና በተከላካይ አማካይነት ተሰልፎ ድንቅ እንቅስቃሴ ያሳየው ዳንኤል ደምሱ የዚህ ጨዋታ ኮከብ በመህምን ተመርጧል።
የአዲስ አበባ ዋንጫ ጨዋታዎች ነገ ሲቀጥሉ በምድብ ለ ባህር ዳር ከተማ ከወላይታ ድቻ በ 08፡00 ፋሲል ከነማ ከጅማ አባ ጅፋር በ10፡00 ይገናኛሉ።