አዳነ ግርማ ወደ ቀድሞ ክለቡ ተመለሰ

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ስማቸው በግምባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው አዳነ ግርማ ከ10 ዓመታት በኋላ ወደ አሳዳጊ ክለቡ ሀዋሳ ከተማ ተመልሷል።

ከ1990ዎቹ መጀመርያ ወደ ሀዋሳ ከተማ ዋናው ቡድን ካደገ በኋላ ሁለት የፕሪምየር ሊግ እና አንድ የኢትዮጵያ ዋንጫን ከቡድኑ ጋር አንስቶ በ1999 ክረምት ነበር ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያመራው። በፈረሰኞቹ ቤትም በዋንጫዎች የታጀበ ድንቅ አስር ዓመታት ከማሳለፉ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ እንድታልፍ ከረዱ ወሳኝ ተጫዋቾች አንዱ መሆን ችሎ ነበር። በሀዋሳ ተከላካይ እና አማካይ ስፍራ ላይ ይጫወተት የነበረው አዳነ በቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አጥቂነት ተለውጦ ሁለት ጊዜ የፕሪምየር ሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ አጠናቋል። 

በመጨረሻዎቹ ሁለት የውድድር ዓመታት ከመደበኛ ተሰላፊነት የራቀው አዳነ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከለቀቀ በኋላ ማረፊያው የቀድሞ ክለቡ ሀዋሳ እንደሚሆን ሲጠበቅ የነበረ ሲሆን በመጨረሻም በሁለት ዓመታት ውል ሀዋሳን ተቀላቅሏል።