ከፍተኛ ሊግ | ኢኮስኮ ስምንት ተጨዋቾችን አስፈርሟል

አምና ስያሜውን ከኢትዮጵያ ውሀ ስፖርት ወደ ኢኮስኮ የለወጠውና በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ የሆነው ኢኮስኮ ዘንድሮ በሚደረገው ውድድር ክፍተት አለብኝ ብሎ ባመነባቸው ቦታዎች ላይ ከፕሪምየር ሊግ እንዲሁም ከከፍተኛ ሊግ ተጨዋቾችን ማዘዋወር ጀምሯል።

አምና በነበረው የውድድር ዓመት ጠንካራ ተፎካካሪ የነበረው ኢኮስኮ በ2011 ከአሰልጣኝ ደግአረገ እንዲሁም ከምክትሉ ሙሉጌታ ጋር በመሆን ቡድኑን በመገንባት ላይ ሲገኝ በዚህ ሂደት ውስጥም ይጠቅሙኛል ያላቸውን ተጨዋቾች ዝውውር ማጠናቀቅ ችሏል። ክለቡ ካደረጋቸው እነዚህ ዝውውሮች ውስጥ ጊዮን መላኩን ከሽረ እንደስላሴ፣ አቤኔዘር ኦቴን ከደቡብ ፖሊስ እና ኡጉታ ኦዶክን ከመከላከያ ያመጣባቸው ዝውውሮች በፕሪምየር ሊጉ ከሚገኙ ክለቦች የተፈፀሙ ናቸው። ኢኮስኮ ከከፍተኛ ሊግ ክለቦች ከፈፀማቸው ዝውውሮች ደግሞ የዲላ ከተማውን ሙና በቀለ ፣  የመቂ ከተማውን ቴዎድሮስ ሰለሞን ፣ የሰበታ ከተማውን ዳንኤል ታደሰ ፣ የሱሉልታ ከተማውን ቶሎሳ ንጉሴ እና የቡራዩ ከተማውን ኢሳይያስ ታደሰ ማስመጣት ችሏል።


ክለቡ ከፈፀማቸው ዝውውሮች መካከል በቡራዩ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ኢሳይያስ ታደሰ እንዲሁም በሱሉልታ ጎልቶ መታየት የቻለውን ሌላኛው አጥቂ ቶሎሳን ማምጣቱ  በዘንድሮው የውድድር ዓመት የአጥቂ መስመሩን በማጠናከር ላይ ትኩረት እንዳደረገ ያሳያል።