በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ሁለተኛ ቀን ውሎ ባህር ዳር እና ፋሲል አሸንፈዋል

በአዲስ አበባ ከተማ  እግር ኳስ ፌደሬሽን አዘጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ (ሲቲ ካፕ) ሁለተኛ ቀን ውሎ የምድብ ሁለት የመጀመሪያ ጨዋታዎች ዛሬ ሲከናወኑ ባህር ዳር ከተማ እና ፋሲል ከነማ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።

8 ሰዓት ላይ ባህር ዳር ከተማ እና ወላይታ ድቻ ተገናኝተዋል። ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ዳዊት አሳምነው የመራው ጨዋታ ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች ወደ ግብ ደርሰው የጠራ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። በ4-3-3 አሰላለፍ ወደ ሜዳ የገቡት የጣናው ሞገዶቹ በአንፃራዊነት ኳስን ተቆጣጥረው ሲጫወቱ የጦና ንቦቹ ደግሞ በ4-4-2 የተጨዋች አደራደር በሜዳቸው አፈግፍገው ጨዋታውን አሳልፈዋል። 

የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ በ15ኛው ደቂቃ የተመለከትን ሲሆን የባህር ዳር የመሃል ተከላካይ አቤል ውዱ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተገኘችውን የቅጣት ምት ፍፁም ተፈሪ ሞክሯት ወደ ውጪ ወጥታለች። ከደቂቃዎች በኋላ የጨዋታውን እንቅስቃሴ ወደ ራሳቸው አድርገው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ባህር ዳሮች ወሰኑ ዓሊ እና ግርማ ዲሳሳን ቦታ በመቀያየር ለማጥቃት ሞክረዋል። ሁለቱ የመስመር ተጨዋቾች ቦታ ከተቀያየሩ በኋላ የተሻሉት ባህር ዳሮች በተለይ ዳንኤል እና ፍቅረሚካኤል የሚጥሏቸው ረጃጅም ኳሶች አደጋ ሲፈጥሩ ታይቷል። 

በ40ኛው ደቂቃ ጃኮ አራፋት እና ግርማ ዲሳሳ አንድ ሁለት ተቀባብለው ለወሰኑ ዓሊ ያቀበሉትን ኳስ ወሰኑ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ እድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ወላይታ ድቻዎች የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩት በሳምሶን ቆልቻ  ጥሩ የግብ ማግባት እድል አግኝተው የነበረ ቢሆንም ሳምሶን ኳሷን አምክኗታል። ከሳምሶን እድል በተጨማሪ በ45ኛው ደቂቃም ድቻዎች በሄኖክ የርቀት ምት ሌላ አጋጣሚ ፈጥረው ኳሷ ኢላማዋን ባለመጠበቋ ግብ ሳያስቆጥሩ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ ባህር ዳር ከተማዎች ተነቃቅተው ወደ ሜዳ በመግባት ጨዋታው እንደተጀመረ በአንድ ደቂቃ ውስጥ ግብ አስቆጥረዋል። ወሰኑ ዓሊ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ከሰበታ ከተማ ዘንድሮ የጣና ሞገዶቹን የተቀላቀለው አዲሱ ፈራሚ ኤሊያስ አህመድ ከወላይታ ድቻ ተከላከዮች ጋር ታግሎ ያገኛትን ኳስ መረብ ላይ አሳርፏታል። አሁንም ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉት ባህር ዳሮች ወደ ግብ በተደጋጋሚ መድረስ የቻሉ ሲሆን ፍሬ ማፍራት ግን ተስኗቸዋል። 


ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በርካታ ለውጦችን ያደረጉት ድቻዎች በተለይ የአጥቂ መስመር ተጨዋቾችን ለውጠው ወደ ሜዳ አስገብተዋል። ቅያሪዎቹም የጠቀማቸው መስሎ በ60ኛው ደቂቃ አስቆጪ የግብ ማግባት ሙከራ አድርገዋል። ባዬ ገዛኸኝ ለአብዱልሰመድ ዓሊ ያሳለፈለትን ኳስ አብዱልሰመድ ከግብ ጠባቂው ምንተስኖት አሎ ጋር  ተገናኝቶ  ኳሷን ግብ ጠባቂው ምንተስኖት አምክኖበታል።
ድቻዎች መመራታቸው ያስቆጫቸው በሚመስል መልኩ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተለየ ከሜዳቸው ወጥተው ሲጫወቱ በአንፃሩ ግን አጨዋወታቸው ለስህተት ቅርብ ሆኖ ዋጋ አስከፍሏቸዋል። ጃኮ አራፋት በ78ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ በአግባቡ ተቆጣጥሮ ግብ በማስቆጠር የቡድኑንም መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል። ባህር ዳሮች መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ካደረጉ በኋላ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው የተጫወቱ ሲሆን ድቻዎች ደግሞ በሙሉ ሃይላቸው ለማጥቃት ሲሞክሩ ነገር ግን የጠራ የግብ ማግባት አድል መፍጠር ሲሳናቸው ታይቷል። ሙሉ 90 ደቂቃው ተጠናቆ በጭማሪ ሰዓት ማራኪ ወርቁ ለአህመድ ዋቴራ አቀብሎት ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ዋቴራ ኳሷን ሳይጠቀምበት የቀረው አጋጣሚ በመጨረሻ ሰዓት የታየ የግብ ማግባት አጋጣሚ ነበር። ጨዋታውም በዚሁ ውጤት በባህር ዳር አሸናፊነት ተጠናቋል።


የዚህ ጨዋታ ኮከብ ተብሎ የተመረጠው የባህር ዳር ከተማው ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ነው።
ከባህር ዳር እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ በመቀጠል በተከናወነው የእለቱ መርሃ ግብር ፋሲል ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር የምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን አከናውነዋል። ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ለቀድሞ ተጨዋቾቻቸው (ከድር ኸይረዲን፣ ሄኖክ ገምቴሳ፣ ይሳቅ መኩሪያ እና ኤርሚያስ ሃይሉ) የማስታወሻ ስጦታ ያበረከቱላቸው ሲሆን ተጨዋቾቹም ምስጋናቸውን ለደጋፊዎቹ አቅርበው ፎቶ ተነስተዋል።


ከአምናው ስብስባቸው ሶስት ተጨዋቾችን ብቻ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ አስገብተው የጀመሩት ጅማ አባጅፋሮች የጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ጥሩ የተንቀሳቀሱ ቢሆንም ደቂቃዎች በገፋ ቁጥር ግን በፋሲሎች ብልጫ ተወስዶባቸዋል። ከአዳማ ከተማ ወደ ፋሲል ከነማ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ያመራው ሱራፌል ዳኛቸው በ16ኛው ደቂቃ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ከመስመር  ወደ መሃል ሰብሮ በመግባት የመጀመሪያ ሙከራ ያደረገ ሲሆን ተጨዋቹ ከርቀት አክርሮ የመታት ኳስ ኢላማዋን በመሳቷ መረብ ላይ ሳታርፍ ቀርታለች። 



ፋሲሎች ከደቂቃዎች በኋላ አብዱረህማን ሙባረክ በአዳማ ሲሶኮ ተጠልፎ የፍፁም ቅጣት ምት ያገኙ ሲሆን ኢዙ አዙካ በ26ኛው ደቂቃ ፍፁም ቅጣት ምቷን ወደ ግብነት ቀይሯት ቡድኑን መሪ አድርጓል። ግብ ያስተናገዱት ጅማዎች ከአንድ ደቂቃ በኋላ ወደ ጨዋታው የሚመለሱበትን እድል በቢስማክ አፒያ አማካኝነት አግኝተው ከዲዲዬ የተቀበለውን ኳስ ቢስማክ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። አሁንም አቻ ለመሆን የሞከሩት ጅማዎች በ35ኛው እና በ40ኛው ደቂቃ በዲዲዬ ለብሪ አማካኝነት ሙከራዎችን ሰንዝረዋል። 

በዚሁ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል ያመሩ ሁለቱ ቡድኖች ከእረፍት መልስ በአንፃራዊነት የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል። ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ሱራፌል ዳኛቸው በቅጣት ምት የፋሲሎችን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ሊያደርግ የሚችልበትን እድል አግኝቶ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂው ዘሪሁን አምክኖበታል። ፋሲሎች ከመከላከል  ወደ ማጥቃት በሚያደርጉት ሽግግር የጅማ ተከላካዮች ተቸግረው የታዩ ሲሆን በተለይ ሱራፌል እና አብዱራህማን የሚያደርጓቸው የመስመር ላይ እንቅስቃሴዎች ፈተና ሆኖባቸው አምሽቷል። በዚሁ የጨዋታ እንቅስቃሴ አብዱራህማን ለኢዙ አዙካ ከመስመር ያሻገረለትን ኳስ ኢዙ ኳስ እና መረብን አገናኝቶ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል። 



ሁለተኛው ግብ ከተቆጠረች ከስምንት ደቂቃዎች በኋላም ሱራፌል የግብ ጠባቂው ዘሪሁንን ስህተት ተጠቅሞ ሌላ የግብ ማግባት እድል ቢፈጥርም ኳሷን የግቡ አግዳሚ መልሷታል። ከዚህ በኋላ ጅማዎች ባላቸው ደቂቃ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሲጥሩ በተለይ  በ75 እና በ76ኛው ደቂቃ ያለቀለት አጋጣሚ አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። አስቻለው ግርማ በ76ኛው ደቂቃ ያደረጋት ነገር ግን የግቡ ቋሚ የመለሳትን ኳስ ፋሲሎች በፍጥነት ወደ ጅማዎች ግብ ክልል ወስደዋት በፋሲካ አስማማው አማካኝነት ወደ ግብ ለመቀየር ጥረት አድርገው ነበር።  



ወደ ጨዋታው ለመመለስ በርካታ ጥረቶችን እያደረጉ የነበሩት ጅማዎች በ80ኛው ደቂቃ ፍላጎታቸውን ያቀዘቀዘ ክስተት ተከስቷል። አክሊሉ ዋለልኝ ሱራፌል ዳኛቸው ላይ በሰራው ጥፋት ሁለቱም ከሜዳ የተሰናበቱ ሲሆን አክሊሉ በቀይ  ካርድ ሱራፌል ደግሞ በጉዳት ወደ መልበሻ ክፍል እና ሆስፒታል አምርተዋል። ጅማዎች የተጨዋች ቁጥር ብልጫ ቢወሰድባቸውም በ84ኛው ደቂቃ በቢስማክ አፒያ በባዶ ከመሸነፍ ያዳናቸውን ግብ አስቆጥረዋል። ግቡን ያስቆጠረው ቢስማክ በጭማሪው ደቂቃ ያለቀለት የግብ ማግባት አጋጣሚ አግኝቶ ቡድኑን ነጥብ አጋርቶ የሚወጣበት እድል አግኝቶ የነበረ ቢሆንም ተጨዋቾ እድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ጨዋታውም በፋሲል ከነማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።



የዚህ ጨዋታ ኮከብ ተብሎ የተመረጠው ማሊያዊው የፋሲል ከነማ ግብ ጠባቂ ሚኬል ሳማኬ ነው።