ካሜሩን 2019| ዋልያዎቹ ዛሬ ምሽት ወደ ኬንያ ይጓዛሉ

ዋልያዎቹ ለ2019 የካሜሩን አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምድቡ አራተኛ እና እጣ ፈንታቸውን የሚወስን እጅግ ወሳኝ ጨዋታቸውን የፊታችን እሁድ ለማድረግ ዛሬ ማምሻውን ወደ ኬንያ ናይሮቢ ያቀናሉ።

የምድብ ሦስተኛ ጨዋታቸውን በትናትናው ዕለት በባህር ዳር አለማቀፍ ስቴዲዮም ቁጥሩ ከፍተኛ በሆነ ተመልካች እና አስደናቂ ድባብ ታጅበው ከኬንያ ጋር ያለ ግብ በአቻ ውጤት የተለያዩት ዋልያዎቹ ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ በመግባት ከሰዓት ላይ የማላቀቂያ ልምምድ በመስራት ምሽት 05:00 ላይ ወደ ናይሮቢ ያመራሉ።

አብርሃም መብራቱ (ኢንስትራክተር) በባህር ዳር በነበራቸው የዝግጅት ቆይታ በቡድኑ ውስጥ ከነበሩት 24 ተጫዋቾች መካከል የቅዱስ ጊዮርጊስ አማካይ ናትናኤል ዘለቀ ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት ከትላንቱ የኬንያ ጨዋታ ውጪ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ሙሉ ለሙሉ ከጉዳቱ ያላገገመ በመሆኑ ዛሬ ወደ ኬንያ ከሚያቀኑት ተጫዋቾች ስብስብ ውጪም ሆኗል። የተቀሩት 23 ተጨዋቾች በሙሉ ግን ወደ ኬንያ ሲያቀኑ በጥቅሉ ከ30 በላይ የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ልዑካን አባላት የሚጓዙ ይሆናል።


ናይሮቢ በሚገኘው ኤምአይኤስሲ ካሳራኒ ስታድየም እሁድ ምሽት 1:00 የሚደረገውን ጨዋታ ሞሪሸሳዊው አህመድ ሔራላል በዋና ዳኝነት ሲመራ የሀገሩ ዜጎች የሆኑት ካቬሌት ራልፍ ፋቢየን እና ሳይሌሽ ጎቢን በረዳትነት ተመድበዋል። አራተኛ ዳኛም ከሞሪሸስ ሲሆን የጨዋታው ኮሚሽነር ከደቡብ ሱዳን ናቸው።