በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ አራተኛ ቀን ጨዋታዎች አባ ጅፋር እና ባህር ዳር አሸንፈዋል

በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ምድብ ለ ዛሬ ሁለት ጨዋታወች በአዲስ አበባ ስታዲየም ተደርገው ጅማ አባጅፋር ወላይታ ድቻን፤ ባህርዳር ከተማ ፋሲል ከነማን በተመሳሳይ 1-0 አሸንፈዋል።

ቀን 9:00 ሰዓት ላይ የተጀመረው የጅማ አባጅፋር እና የወላይታ ድቻ ጨዋታ በጅማ አባጅፋር 1-0 አሸናፊነት ተደምድሟል። የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ አሰልቺ እንቅስቃሴ እና ጥቂት ሙከራዎች የታጀበ ሲሆን ከጨዋታው እንቅስቃሴ ይልቅ 7ኛው ደቂቃ ላይ የእለቱ ዋና ዳኛ ተካልኝ ለማ እና ረዳቶቻቸው ከወላይታ ድቻ ጋር ተቀራራቢ ትጥቅ በመልበሳቸውና በሜዳ ላይ ተመሳስሎ በመታየቱ ወደ መልበሻ ክፍል ገብተው ሊቀይሩ የተገደዱበት ሂደት ትኩረት ስቧል። ከቡድን እንቅስቃሴ ይልቅ በግል በተሻለ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት የመስመር አጥቂው አስቻለው ግርማ እና በክለቡ የመከራ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ቢስማርክ አፒያ እንቅስቃሴ እና ጥረታቸው የሚጠቀስ ነበር። 


ወላይታ ድቻዎች ደግሞ የግብ እድሎች በመፍጠር ረገድ ተሽለው ታይተዋል። 10ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ ገዛኸኝ ወደ ግብ ክልሉ ተጠግቶ የመታት እና ኢላማዋን ሳጠብቅ የወጣችሁ ኳስ የመጀመሪያ ሙከራ ስትሆን 15ኛው ደቂቃ ላይ ሳምሶን ቆልቻ በመስመር በኩል ያሻገረለትን ኳስ ባዬ ገዛኸኝ በቀጥታ ወደ ግብ ሲመታው የግቡን ቋሚ ብረት ታካ ወታበታለች። 19ኛው ደቂቃ ላይ ጅማ አባ ጅፋርን ለቆ ድቻን የተቀላቀለው ሄኖክ ኢሳያስ ከግብ ክልል ውጭ አክርሮ የመታውን ኳስ በዘሪሁን ታደለ አስደናቂ ብቃት ያዳነበት ሙከራም የሚጠቀስ ነበር፡፡


በሁለተኛው አጋማሽ በተመሳሳይ ሳቢ ያልሆነ እንቅስቃሴ የታየ ሲሆን ጅማ አባ ጅፋሮች ከመጀመሪያው አጋማሽ ተሻሽለው ቀርበዋል። 59ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ይሁን እንደሻው በቀኝ መስመር በኩል ያሻገረውን ኳስ አዳማ ሲሶኮ በግንባር መትቶ የግቡ ብረት ሲመልሳት በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው አስቻለው ግርማ አስቆጥሮ አባ ጅፋርን መሪ ማድረግ ችሏል። 70ኛው ደቂቃ ላይ የጅማ አባጅፋሩ ግብ ጠባቂ ዘሪሁን ታደለ ከወላይታ ድቻ የግብ ክልል የተሻገረን ኳስ ከመስመር ወጥቶ ይዟል በሚል የድቻ ተጫዋቾች ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ዳኛው በዝምታ ማለፋቸውም አስገራሚ ክስተት ነበር። 

ግብ ለማስቆጠር በመጨረሻወቹ ደቂቃዎች ላይ ማጥቃት ላይ ትኩረት ያደረጉት ድቻዎች በሳምሶን  ቆልቻ እና ቸርነት ጉግሳ አማካኝነት ሙከራዎች ሲያደርጉ በጅማ በኩል አስቻለው ግርማ እና ቢስማርክ አፒያ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት በጅማ አባጅፋር 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡


ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የጅማ አባጅፋሩ የመስመር ተጫዋቾች አስቻለዉ ግርማ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል፡፡

11:30 በጀመረው ሁለተኛ ጨዋታ ባህርዳር ከተማን ከፋሲል ከነማ አገናኝቷል። ከመጀመሪያው ጨዋታ ይልቅ በርካታ ደጋፊዎች በታደሙበት በዚህ ጨተታ የባህር ዳር ከተማ የእንቅስቃሴ የበላይነት የታየበት ነበር። ዳንኤል ኃይሉ ከርቀት መቶ የግቡ ብረት የመለሰበት የባህር ዳር ከተማ ቀዳሚ አጋጣሚ ስትሆን 11ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ታዳጊው ናትናኤል ወርቁ መሀል ለመሀል የሰጠውን ኳስ በቀላሉ አብዱራህማን ሙባራክ  ያመከናት አጋጣሚ ደግሞ የፋሲል ከተማ የመጀመሪያ እድል ነበረች። ከደቂቃዎች በኋላ አጼዎቹ በፋሲል አስማማው አማካኝነት ሌላ አጋጣሚን ቢያገኙም ግብ ጠባቂው ምንተስኖት አሎ አድኖበታል።

ከዚህች ሙከራ በኃላ ፍፁም የባህርዳር ከተማ ብልጫን ባየንበት ቀሪ ደቂቃዎች በኤልያስ አህመድ እንዲሁም በመስመር በኩል የተሳካ አጋጣሚን ሲፈጥር በነበረው ግርማ ዲሳሳ አማካኝነት በተደጋጋሚ የፋሲልን የግብ በር ፈትሸዋል። 24ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል ኃይሉ ከግርማ የተሻገረለትን ኳስ ሞክሮ ጀማል ጣሰው በቀላሉ ሲይዝበት አስናቀ ሞገስ በረጅሙ የላካትን ኳስ ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው እና አምበሉ ያሬድ ባዬ ባለመናበባቸው ምክንያት ጃኮ አራፋት አጋጣሚ ማግኘት ቢችልም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ከአንድ ደቂቃ በኃላ ጃኮ አራፋት ያገኛትን ኳስ በቀጥታ መቶ ወደ ውጭ ስትወጣበት 28ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ተከስተ በባህርዳር ከተማው የመስመር አጥቂ ግርማ ዲሳሳ ላይ በግብ ክልል ውስጥ በሰራበት ጥፋት የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ቶጓዊው አዲሱ የባህር ዳር ከተማ አጥቂ ጃኮ አራፋት ወደ ግብነት ለውጧት የመጀመሪያው አጋማሽ በባህርዳር ከተማ 1-0 መሪነት ተጠናቋል። 


ከእረፍት መልስ ባህርዳር ከተማ ቀዝቀዝ ብሎ ሲቀርብ ፋሲሎች ቅያሪዎቹ ለውጦችን ፈጥረውለት ተሽሎ ቀርቧል። የጎላ ሙከራ ያልታየበት የሁለተኛው አጋማሽ በእንቅስቃሴ የፋሲል የበላይነት የታየበት ቢሆንም አፄዎቹ የሚያገኟቸውን ኳሶች በአግባቡ ያለመጠቀማቸው ዋጋ አስከፍሏቸዋል። በ78ንኛው ደቂቃ ላይ የባህርዳር ከተማ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች ኳስ ለማራቅ ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት በሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ በመንካታቸው የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ተከላካዩ እና አምበሉ ያሬድ ባዬ ቢመታውም የባህር ዳር ከተማው ግብ ጠባቂ ምንተስኖት አሎ ያዳነበትም ፋሲል አቻ ለመሆን የሚያስችል ወርቃማ አጋጣሚ ነበር።

ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር በባህር ዳር 1-0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ የባህር ዳር ከተማው ወንድሜነህ ደረጀ የጨዋታው ኮከብ በመባል ተመርጧል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ከአንድ ቀን እረፍት በኋላ ቅዳሜ እና እሁድ በመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች ሲቀጥል ቅዳሜ በ8:00 ኤሌክትሪክ ከ አዳማ ከተማ፣ በ10:00 ኢትዮጵያ ቡና ከ መከላከያ ይጫወታሉ። እሁድ ደግሞ በ8:00 ባህር ዳር ከተማ ከ ጅማ አባ ጅፋር፣ በ10:00 ፋሲል ከነማ ከ ወላይታ ድቻ የሚጫወቱ ይሆናል።