በዓምላክ እና ረዳቶቹ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታን ይመራሉ

ነገ ከሚደረጉ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች መካከል አንዱ በኢትዮጵያዊያን ዳኞች ይመራል።

በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው ቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ የአህጉሪቱ ብሔራዊ ቡድኖች የማጣሪያ ጨዋታዎቻቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ። ኢትዮጵያም በውድድሩ እየተካፈለ ከሚገኘው ብሔራዊ ቡድኗ በተጨማሪ በዳኞቿ አማካይነትም እየተሳተፈች ትገኛለች። በዚህ ረገድ በዋነኝነት የሚነሳው ደግሞ በያዝነው ዓመት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታን ጨምሮ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ በርከት ያሉ ጨዋታዎችን የዳኘው በዓምላክ ተሰማ ነው።

በአምላክ በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ካሜሩን ከሞሮኮ እንዲሁም ኢስዋቲኒ ከቱኒዚያ ያደረጉትን ጨዋታዎች በመሀል ዳኝነት የመራ ሲሆን ነገ 1፡00 ላይ ሴኔጋልን ከሱዳን በሚያገናኘው የምድብ አንድ ሶስተኛ ጨዋታ ላይም የመዳኘት ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ዳካር በሚገኘው በሊዮፖልድ ሴዳር ሴንጎር ስታድየም የሚደረገውን ይህን ጨዋታ ከበዓምላክ ጋር ሁለቱን የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች አብሮ የዳኛው ተመስገን ሳሙኤል እና ትግል ግዛው በረዳት ዳኝነት እንዲሁም ቴዎድሮስ ምትኩ በአራተኛ ዳኝነት እንደሚመሩትም ታውቋል።