የደቡብ ካስቴል ዋንጫ በሦስት ክለቦች መካከል ብቻ ይካሄዳል

የመካሄዱ ነገር እርግጥ ያልነበረው የደቡብ ካስቴል ዋንጫ የፊታችን ዕሁድ በሶስት ክለቦች መካከል መካሄድ ይጀምራል፡፡

ለአምስት ዓመታት በካስቴል ቢራ ስፖንሰር የተደረገው እና በደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን መሪነት ላለፉት ሁለት ዓመታት የተካሄደው የደቡብ ካስቴል ዋንጫ ከስድስት በላይ ክለቦችን እያሳተፈ የነበረ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ዘንድሮም በተመሳሳይ ውድድሩ በክልሉ ባሉ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች እና ተጋባዦች መካከል ከጥቅምት 1 እስከ 10 ይደረጋል ተብሎ ቢጠበቅም ካለፈው ዓመት አንፃር ተሳታፊ ክለቦች ፍቃደኝነታቸው እጅጉን የቀነሰ በመሆኑ የመካሄዱ ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ቆይቷል፡፡ በቅድሚያ ድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡናን በተጋባዥነት እንዲሁም ወላይታ ድቻን ‘ ሲዳማ ቡናን እና ሀዋሳ ከተማን አዲስ አዳጊው ደቡብ ፖሊስን ጨምሮ ለማካሄድ የታሰበ ቢሆንም ወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ በትግራይ ዋንጫ በመሳተፋቸው እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡናም በአማራ ዋንጫ ላይ ይሳተፋሉ በመባሉ ምክንያት ነበር የውደደሩ መካሄድ ጉዳይ አጠያያቂ የሆነው፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ ውድድሩ ከጥቅምት 4-10 በሀዋሳ ከተማ በሶስት ክለቦች መካከል ብቻ እንደሚከናወን የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን ፅ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ወልደሚካኤል መስቀሌ በተለይም ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሰረት ሲዳማ ቡና ‘ ሀዋሳ ከተማ እና ደቡብ ፖሊስን የሚያሳትፈው የዘንድሮው የደቡብ ካስቴል ዋንጫ የፊታችን ዕሁድ ዘጠኝ ሰአት ላይ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ሀዋሳ ከተማ ከደቡብ ፓሊስ በሚያደርጉት የመክፈቻ ጨዋታ በይፋ ይጀመራል፡፡ በተያያዘ ዜናም በደቡብ ክልል የሚገኙ ከ10 በላይ የከፍተኛ ሊግ ክለቦችን የሚያሳትፈው የደቡብ ክልል የከፍተኛ ሊግ ካስትል ዋንጫ ውድድር ከጥቅምት 18 ጀምሮ በዱራሜ ከተማ እንደሚደረግ ፌድሬሽኑ አሳውቋል፡፡