በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የዛሬ ውሎ ቀሪ የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚዎች ተለይተዋል

የምድብ ለ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች በተደረጉበት የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ባህር ዳር ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር አላፊ ሆነዋል።

08፡07 ላይ በቅድሚያ የተደረገው ጨዋታ የምድቡን መሪ ባህርዳር ከተማን እና ሶስት ነጥቦች ይዞ ሶስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ጅማ አባ ጅፋርን ያገናኘ ነበር። በፈጣን እንቅስቃሴ የጀመረው ይህ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በቶሎ በተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ዙሪያ የተገኙባቸውን ቅፅበቶች አሳይቶናል። የአባጅፋሩ የፊት አጥቂ ቢስማርክ አፒያ በነዚሁ ጊዜያት ከሌሎች የተሻሉ ሁለት የማግባት አጋጣሚዎችን ቢያገኝም ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል። የጨዋታው ፍጥነት እየቀነሰ በመጣባቸው ቀጣይ ደቂቃዎች ደግሞ የባህርዳሮች ተደጋጋሚ ጥቃት ታይቷል። ቡድኑ ከአማካይ መስመሩ በሚነሱ ኳሶች በጅማ ሜዳ ላይ ሆኖ ጫናን ሲፈጥር የቆየ ሲሆን የመስመር አጥቂዎቹ ፍጥነት  ደግሞ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን እንዲያደረግ ረድቶታል። 16ኛው ደቂቃ ላይ ግርማ ዲሳሳ ከግራ መስመር የላከው እና ፍቃዱ ወርቁ በሸርተቴ ለማስቆጠር ሞክሮ ያልተሳካለት እንዲሁም ፍቃዱ በድጋሜ 26ኛው ደቂቃ ላይ የተላከለትን ረጅም ኳስ በግራው የጅማ ግብ ቋሚ ለማስቆጠር ተቃርቦ የነበረበት አጋጣሚ የሚጠቀሱ ናቸው። ከነ ኤልያስ ማሞ አጫጭር ቅብብሎች በተጨማሪ በረጃጅም ኳሶች አጥቂዎቻቸውን ለማግኘት ሲሞክሩ የነበሩት ጅማዎች በበኩላቸው በዲዲዬ ለብሪ እና አስቻለው ግርማ በኩል ወደ ውስጥ ለመግባት ያደርጉት የነበረው ጥረት አደጋ መፍጠር ሳያስችላቸው ነበር የመጀመሪያው አጋማሽ የተጠናቀቀው።


ቡድኖቹ ከመልበሻ ቤት ሲመለሱ ጅማ አባ ጅፋሮች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተለየ ጠንክረው በይሁን እንዳሻው የሚመራው የአማካይ ክፍላቸውም በሚገባ ተፅዕኖው ጨምሮ እና በቀኝ መስመር አድልተው ጫና ሲፈጥሩ ታይተዋል። ዲዲዬ ለብሪ በቀኝ መስመር ያሻማው እና ተቀይሮ የገባው ኤርሚያስ ኃይሉ በግንባሩ ለማግኘት የሞከረው ኳስ ደግሞ የቡድኑ የመጀመሪያ ሙከራ ነበር። 50ኛው ደቂቃ ላይም በድጋሜ በረጅም ወደሳጥን የተላከ ኳስ ቢስማርክ አፒያ በደረቱ አብርዶለት ዲዲዬ ቢሞክርም ኳስ በግቡ አግዳሚ ተመልሳለች። ባህርዳሮች ምንም እንኳን በዚህ መልኩ ጫና ውስጥ ቢገቡም ግርማ ዲሳሳ በተሰለፈበት የግራ መስመር ጥሩ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን አግኝተው በፍጥነት በጅማ ሳጥን ውስጥ ቢገኙም አጋጣሚዎቹን ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል። በርካታ የተጨዋች ቅያሪ ያደረጉት ሁለቱ ቡድኖች በቀሩት ደቂቃዎች በመስመር ተሳላፊዎቻቸው ላይ ተመስርተው ጥቃቶችን የሰነዘሩ ቢሆንም የመጨረሻ ዕድሎች ግን የተፈጠሩት በጥቂት አጋጣሚዎች ነበሩ። የባህርዳሩ አጥቂ ጃኮ አራፋት እና የጅማው ቢስማርክ አፒያ ዕድሎቹን መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። ከዚህ ውጪ የጅማዎቹ ብሩክ ገ/አብ በግራ መስመር የባህርዳሩ ማራኪ ወርቁ ደግሞ በቀኝ መስመር ለየቡድኖቻቸው ሙከራዎች መነሻ ሲሆኑ ተስተውሏል። መልካም ፉክክር የታየበት የሁለቱ ቡድኖች የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታቸውም በዚህ መልኩ የጅማ አባ ጅፋሩን ይሁን እንዳሻውን የጨዋታው ኮከብ አድርጎ 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል። 

10፡25 ሲል የጅመረው የምድብ ለ የመጨረሻ ጨዋታ ፋሲል ከነማን ከወላይታ ድቻ ያገናኛ ነበር። በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በአመዛኙ የፋሲሎች የበላይነት የታየበት ተንፀባርቆበታል። የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን በመውሰድ ለተጋጣሚያቸው የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ቀርበው የተንቀሳቀሱት አፄዎቹ 8ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው ከኤዱ ቤንጃሚን ጋር ተቀባብሎ በመግባት ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ ሚዛኑን ከሳተበት አጋጣሚ ጀምሮ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። ወደ አማካይ ክፍሉ በጥልቀት እየገባ ሲጫወት የተስተዋለው የመስመር አጥቂው ሱራፌል 29ኛው ደቂቃ ላይ ያደረገው የረጅም ርቀት የቅጣት ምት ሙከራ እንዲሁም ከአንድ ደቂቃ በኋላ ፋሲል አስማማው በቀኝ መስመር ከታሪክ ጌትነት ጋር ተገናኝቶ ያመከነው ኳስ ተጠቃሽ ሲሆኑ 34ኛው ደቂቃ ላይም የቡድኑ ተሰላፊዎች በአጫጭር ቅብብሎች ተበራክተው በድቻ ሳጥን ከተገኙ በኋላ ያልተጠቀሙበት ዕድልም ከጠንካራዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ሙከራዎች የሚካተት ነው። 

በተጋጣሚያቸው ብልጫ የተወሰደባቸው ወላይታ ድቻዎች በበብዛት በራሳቸው የሜዳ አጋማሽ ላይ ለመቆየት የተገደዱ ሲሆን ካገኟቸው የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶችም በቂ ዕድሎችን መፍጠር አልቻሉም። 41ኛው ደቂቃ ላይ ብቻ ከያሬድ ባየህ የቅብብል ስህተት በተገኘ አጋጣሚ ፍፁም ተፈሪ ወደ ሳጥን የጣለውን ኳስ ቸርነት ጉግሳ አክርሮ ሞክሮ ሚኬል ሳማኬ ያወጣበት ሙከራ የአጋማሹ እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር። 
የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ገፅታ ከመጀመሪያው የተለየ ሆኗል። ከፍተኛ ብልጫ ተወስዶባቸው የነበሩት ወላይታ ድቻዎች ፍፁም ተቀይረው በተለይም በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች የበላይነቱን አግኝተዋል። በቀኝ መስመር አማካዩ ቸርነት ጉግሳ እንቅስቃሴ ላይ የተመሰረተው የድቻዎች ጥቃት ከፈጠረው ሁለት የመጨረሻ የግብ ዕድሎችም አንደኛው በሳማኬ መረብ ላይ አርፏል። ጎሉ 60ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ወደ ሳጥን የላከውን ኳስ ፀጋዬ በቀጥታ መትቶ ያስቆጠረው ነበር። 


ከስድስት ደቂቃዎች በኋላም ቸርነት ተመሳሳይ ኳስ መሬት ለመሬት ወደ ሳጥኑ ቢያደርስም ሳምሶን ቆልቻ በማይታመን መልኩ አምክኖታል። ድቻዎች እንደአጀማመራቸው ባይሆንም በፋሲል የሜዳ ክልል ላይ መገኘታቸውን በቀጠሉበት ጨዋታ ፋሲሎችም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር መሞከራቸው አልቀረም። ነገር ግን ከመጀመሪያው ይልቅ ረዘም ያሉ ኳሶችን ወደ ፊት መጣል የቡድኑ ተመራጭ መንገድ ሆኖ ይታይ ነበር። በዚህ መልኩ የአቻ ውጤት ወደ ግማሽ ፍፃሜው ይወስዳቸው የነበሩት አፄዎቹ ከሰይድ ሁሴን እና ሱራፌል ዳኛቸው በሚነሱ ኳሶች ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ቢሰነዝሩም ተፈላጊዋን ጎል ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል። 69ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ከመሀል ሜዳ ባሳለፈው ኳስ አብዱርሀማን አክርሮ በመምታት ወሳኟን ግብ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ ታሪክ ጌትነት መልሶበታል። ግብ ተባቂው በመጨረሻ ደቂቃ ላይም ፋሲልን ለማሳለፍ ትቃርባ የነበረች ሌላ ጠንካራ ሙከራም አድኖ ወላይታ ድቻ ጨዋታውን 1-0 እንዲያሸንፍ ረድቷል። 


ለብቸኛዋ ግብ መገኘት ቁልፍ ሚና የተወጣው ወጣቱ የመስመር አማካይ ቸርነት ጉግሳ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ሲመረጥ በዕለቱ በተመዘገቡት ውጤቶች ባህርዳር ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር ወደ ግማሽ ፍፃሜው ማለፍ ችለዋል።