የትግራይ ዋንጫ በመቐለ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

ከመስከረም 26 ጀምሮ በ6 ክለቦች መካከል በመቐለ ሲከናወን የቆየው የትግራይ ዋንጫ በዛሴው ዕለት በተከናወነ የፍፃሜ መርሐ ግብር ተጠናቋል። መቐለ ሰባ እንደርታም ተጋባዡ ድሬዳዋ ከተማን በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል።

ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት ይህ ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ማራኪ ጨዋታ እና በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎችም የታየበት ነበር። በመጀመርያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ የተከላካይ ክፍላቸው በእጅጉ ወደ መሃል ሜዳ በማስጠጋት ለመከላከል የመረጡበትና እና ጥሩ የኳስ ፍሰት ያሳዩበት ነበር። ወሰኑ ማዜ ከሳጥኑ ጠርዝ አካባቢ ቅጣት ምት መትቶ ለጥቂት በወጣችው ሙከራ የተጀመረው ጨዋታው ብዙም ሳይቆይ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች ተስተናግደዋል። በመቐለ በኩል ጋብርኤል አህመድ ከስዩም ተስፋዬ የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት የወጣችው እና ሃይደር ሸረፋ ከርቀት አክርሮ መቶ ለጥቂት የወጣችው ኳስ ይጠቀሳሉ።


ከ10ኛው ደቂቃ በኋላ በነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ ድሬዎች በቁጥር ጥቂት የሆኑ ተጫዋቾች በመጠቀም ከመቐለ የአማካይ ተጫዋቾች መካከል የሚገኘው የመቀባበያ መስመር በመዝጋት እና ፍጥነት የተሞላበት ጫና በመፍጠር ለመጫወት ሞክረዋል። ምንም እንኳ አጨዋወቱ በብዙ መንገድ የተዋጣለት ነበር ባይባልም በመቐለ አጨዋወት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ሲያሳርፍ እና ቡድኑ የሚያጠቃበት መንገድ እንዲቀይር ያስገደደ ነበር። በመሃል ሜዳ በብዛት የማይንቀሳቀሰው የድሬዳው የመሃል ሜዳ ጥምረት አልፈው መሃል ለመሃል ለማጥቃት የተቸገሩት መቐለዎች የሚያጠቁበት መንገድ በመቀየር በሁለቱም የመስመር አማካዮቻቸው ሳሙኤል ሳሊሶ እና አማኑኤል ገ/ሚካኤል በመጠቀም ማጥቃት ሲጀምሩ አንድ ያለቀለት የጎል እድል እና ጎል ማግኘት ችለዋል። ሀይደር ሸረፋ ከሳሙኤል ሳሊሶ የተሻገረችለት ኳስ ፍሬው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ኳስዋ ከፍሬው በላይ ከፍ አድርጎ ልኳት ዘነበ ከበደ ከመስመሩ ያዳናት ኳስ በተጠቀሰው አጨዋወት ከተገኙት ሙከራዎች አንዷ ናት።


በ19ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳሊሶ ከመስመር ይዟት የገባው ኳስ አክርሮ በመምታት መቐለን መሪ ማድረግ ችሏል። ጎል ካስተናገዱ በኋላ የአቻነት ጎል ለማግኘት በአንፃራዊነት የተሻለ ለማጥቃት ተጭነው የተጫወቱት ድሬዎች ሁለት ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች ኣድርገው ነበር። ኃይሌ እሸቱ ከመስመር አሻምቷት ከግቡ አቅራብያ የነበረው ኪሜይኒ ያልተጠቀመባት እና ራምኬል ሎክ በተመሳሳይ ቦታ አሻምቶ የመቐለ ተጫዋቾች እንደምንም ተረባርበው ያወጧት ኳስ ትጠቀሳለች። በ41 ደቂቃ ላይ ኣሞስ ኣቼምፖንግ በ ሳጥን ውስጥ በሰራው ጥፋት የተገኘችውን ፍፁም ቅጣት ምት ፍቃዱ ደነቀ በቀድሞ ክለቡ ላይ በማስቆጠር ድሬዳዋ ከተማዎችን አቻ ማድረግ ችሏል። በመቐለዎች በኩልም ግቧ ከተቆጠረችባቸው በኋላ ድጋሚ የሚመሩበት እድል በሁለት አጋጣሚዎች  አግኝተው ነበር። በተለይም ጋብርኤል አህመድ  ሚካኤል ደስታ ያሻማውን  ኳስ ተጠቅሞ በግንባሩ በመግጨት ፍሬው ጌታሁን በሚገርም ብቃት ያዳናት ትጠቀሳለች።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመርያው አጋማሽ በፍጥነቱ ዝግ ያለ እና የመቐለ ሰባ እንደርታ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የታየበት ነበር። በመጀመያዎቹ 10 ደቂቃዎች በራሳቸው የሜዳ ክልል የኳስ ቁጥጥር በመያዝ ጊዜያቸውን ያሳለፉት መቐለዎች በዛ ፍሰት ወደ ድሬ ሳጥን ዘልቀው መግባት ቢከብዳቸውም ጥቃት ከመሰንዘር አልቦዘኑም። ጥረታቸው ተሳክቶም በ57ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ያሻማው የማዕዘን ምት የድሬ ተከላካዮች ቢጨርፉትም በጎሉ ጫፍ በኩል የነበረው ጋብርኤል አህመድ ጨርፎ መቐለን መሪ ማድረግ ችሏል። ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ አቻ ለመሆን 2 ደቂቃ ብቻ የፈጀባቸው ድሬዎች ተቀይሮ ገብቶ ጥሩ እንቅስቃሴ ያረገው ሐብታሙ ወልዴ የግብ ጠባቂው መውጣት ተከትሎ አክርሮ መቶ ማራኪ ግብ በማስቆጠር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። በጨዋታው ከቆሙ ኳሶች ብዙ የግብ እድሎች የፈጠሩት መቐለዎች በ67 ደቂቃም በአንተነህ ገ/ክርስቶስ በኩል ጎል አግኝተዋል። ተጫዋቹ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ያሻማለትን ኳስ ተጠቅሞ በማግባት ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ድሬዎች ተቀይረው የገቡት ኃይሌ እሸቱ እና ዮናታን ከበደ ቀይረው በማስወጣት ጨዋታ ለመቀየር ቢሞክሩም በጨዋታው ይህ ነው የሚባል ለውጥ ማምጣት አልቻለም። እንዳውም በ90+1ኛው ደቂቃ ላይ የድሬ ተከላካዮች በሳጥን ውስጥ ጥፋት መስራታቸውን ተከትሎ የተሰጠውን ቅጣት ምት አማኑኤል ገ/ሚካኤል አስቆጥሮ ቡድኑ ጨዋታውን 4-2 እንዲመራ አስችሏል። ጨዋታውም በዚሁ ውጤት ተጠናቋል። 

ከፍፃሜው በፊት በተከናወነው የደረጃ ጨዋታ ደደቢት እና ሽረ እንዳሥላሴ በመደበኛው ክፍለ ጊዜ 1-1 አጠናቀው በተሰጠው የመለያ ምት ደደቢት 4-3 አሸንፎ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል።