ሎዛ አበራ እና ቱቱ በላይ በስዊድን…

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ መጠናቀቂያ ሰሞን ለሙከራ ወደ ስዊድን በማምራት ከንግስባካ ክለብን መቀላቀል የቻሉት ሎዛ አበራ እና ቱቱ በላይ ከክለባቸው ጋር ስኬትን ማጣጣም ችለዋል። የሁለቱ ተጨዋቾች ክለብ የሆነው ከንግስባካ በስዊድን ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን (ኤልታታ) ሁለት ጨዋታ እየቀረው ወደ መጀመሪያው ዲቪዚዮን (ዳማልቫንስከን) ማደጉን አረጋግጧል። ወደ ስዊዲን ለሙከራ ያቀኑት እና በከንግስባካ ከሙከራ ውጭ ፊርማቸውን ያላኖሩት ሁለቱ ኢትዮጵያዊያን በክለባቸው በሁለተኛው እና በዋናው ቡድን ውስጥ እየተፈራረቁ እየተጫወቱ ይገኛሉ። ሎዛ እና ቱቱ በሁለተኛው ዙር ክለቡን በመቀላቀላቸው ምክንያት በፍጥነት መፈረም ባይችሉም ውጤታማ ጊዜን እያሳለፉ ይገኛሉ።

በመጀመሪያውም በሁለተኛውም ቡድኖች ተሰልፋ መጫወት የቻለችው ሎዛ አበራ በ13 ጨዋታዎች 9 ግቦችን አስቆጥራለች። ክለቡ ወደ ላይኛው ዲቪዚዮን ማደጉን ተከትላ በትዊተር ገጿ ደስታዋን የገለፀችው የፊት አጥቂዋ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋርም ቆይታ አድርጋለች። በሰጠችው አስተያየትም ” እኔና ቱቱ ይህንን ስኬት ከክለባችን ጋር ማጣጣም በመቻላችን ደስተኛ ነኝ። ሁለት ጨዋታ እየቀረን ወደ ዋናው ሊግ ማደግ ችለናል። እኔም ለዋናው ቡድን ተሰልፌ 7 ጨዋታ በማድረግ 4 ጎሎች አስቆጥሬያለሁ። በጁኒየር (ሁለተኛ) ቡድኑም በ6 ጨዋታዎች 5 ጎሎች አሉኝ። ሰፋ ያለ ጊዜን በዋናው ቡድንም ሆነ በታችኛው እያሳለፍኩ ነው። ቱቱም ቢሆን እየተጫወተች ትገኛለች ፤ ከተጠባባቂነት በመነሳት ጥሩ ነገርን እየሰራች ነው። በኩንግስባካ ዋናው ቡድንም ውስጥ ቢሆን አልፎ አልፎ ትገባለች። እኔም በሲኒየር ቡድኑ የተሻለ ጨዋታ አድርጊያለሁ። ጥሩ እና አሪፍ ነው ብዬም አስባለሁ ” ብላለች።

ተቀይራ እየገባች ለሁለተኛው ቡድን ሦስት ግቦች ያስቆጠረችው ቱቱ በላይም ያላትን ሀሳብ ስትሰጥ ” እያደረግን ያለነው ነገር አስደስቶኛል። ከጠበቅኩት በላይ ነው። ለቡድናችን ጥሩ ነገር አድርገናል ብዬ አስባለሁ። ለዚህም ፈጣሪን አመሰግናለሁ። ከቡድኑ በመጣንበት ዓመት ማሰለፋችን ደስተኛ አድርጎኛል በቡድኑ ውስጥ የተሳካ ጊዜ እንደሚኖረንም አልጠራጠርም። ይህን እንዳደርግ የረዳኝን ፈጣሪዬን ማመስገን እፈልጋለሁ” ብላለች::

በኢትዮጵያ የነበራትን የግብ ማስቆጠር ብቃት በስዊድንም በመቀጠል ላይ የምትገኘው ሎዛ አበራ በሀገራችን እና በስዊድን ሊግ መካከል ስላሉ ልዩነቶች ተከታዩን ሀሳብ ሰንዝራለች። ” እዚህ የሚለዩት አናሳ ውጤት ያላቸው ቡድኖችም ይሁኑ ትልልቆቹ ቡድኖች ጠንካራ ነገር ያላቸው መሆኑ ነው። በአቅማቸው እና ፊትነሳቸው ቤስቱም ሆነ ቤንቹ ጥሩ ነገር ለማሳየት ይጥራሉ። ሁሉም ክለቦች ደስ የሚል አቅም ነው ያላቸው። በታክቲኩ ረገድ እኔና ቱቱንም ሲያዩ ባለን ነገር ያበረታቱናል። አመለካከታቸው ሁሌም ደስ ይላል። የሚሰጡህ አስተያየት እና ማበረታት የተለየ ነው። ከኛ ሀገር የሚለየው ለሴቶች የተሰጠው ትኩረት ከፍ ማለቱ ነው። በዲቪዚዮን የተከፈለ በሴት ብቻ ስድስት ሊግ አላቸው። ይህም ለሴቶች ያላቸውን ትኩረት ያሳያል። የሚገርመው ሌላው ደግሞ ለምሳሌ የእንግሊዝ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ውድድር በቴሌቪዥን ሲታይ ወንዶችን ከማየት ሴቶችን በየቦታው እየከፈቱ ያያሉ። ሴቶችን ያበረታታሉ። ለዚህም ነው ያደጉት። ከዛ ውጭ ከልጅነታቸው ጀምሮ ስለሚሰሩ ሰልጥነው አድገው ሰለሚመጡ በፍፁም አንገናኝም። እኛ ብንሰራ በርግጠኝነት እንበልጣቸዋለን። ጥንካሬ እና ፍጥነት ልዩነቶቻችንን ያሳያሉ። እኛ በእግር ኳስ ዕውቀት እንሻላለን ግን ጠንካራ ስራ ላይ በጣም ይቀረናል።”

ሎዛ እስካሁን በቋሚነት ለክለቡ ስላለመፈረማቸው ጉዳይ ደግሞ ይህን ብላለች። ” እኛ ወደዚህ የመጣነው በዋናው ቪዛ አይደለም ፤ በቱሪስት ቪዛ ነው። ስለዚህ ከመጫወት ውጭ ምንም ነገር ለጊዜው የምናደርገው ነገር አይኖርም። ሊጋቸው እስከ ኦክቶበር ይቆያል። ከጨረስን በኋላ በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰን ለቀጣዩ ዓመት ነው ገና የምንፈርመው። የስራ እና የመኖሪያ ፍቃድ እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን ካሟላን በኃላ የክለቡ አባል እንሆናለን። ” ብላለች።


በቴዎድሮስ ታከለ እና ብሩክ ገነነ