የአሸናፊዎች አሸናፊ እና የአዲስ አበባ ዋንጫ የፍፃሜ ቀን ለውጥ ተደርጎበታል

የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ እና የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የፍፃሜ ቀናት እንዳይጋጩ ሽግሽግ ተደርጎባቸዋል። 

ዓመታዊው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ከመስከረም 26 ጀምሮ   እየተካሄደ ይገኛል። ውድድሩ ነገም በግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች የሚቀጥል ሲሆን በሳምንቱ መጨረሻ እንደሚገባደድም መርሀ ግብር ወጥቶለት ነበር። ነገር ግን ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መጀመር አንድ ሳምንት አስቀድሞ የሚከናወነው የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ የጨዋታ ዕለት ጋር መገጣጠሙ አነጋጋሪ ሆኖ ቆይቷል። ከዚህ በተጨማሪም የአምና የፕሪምየር ሊግ እና የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊዎች ጅማ አባ ጅፋር እና መከላከያ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ መድረሳቸው ጉዳዩን ያወሳሰበው ይመስል ነበር።

የተፈጠረውን የመርሀ ግብር መገጣጠም ለማስተካከልም በሁለቱም ውድድሮች የፍፃሜ ቀናት ላይ ሽግሽግ ተደርጓል። በዚህም መሰረት የአዲስ አበባ ዋንጫ የፍፃሜ እና የደረጃ ጨዋታዎች በአንድ ቀን ቀደም ብለው ቅዳሜ ጥቅምት 10 በ9፡00 እና በ11፡00 የሚከናወኑ ይሆናል። የአሸናፊዎች አሸነፊው ጨዋታ ደግሞ በሁለት ቀናት ወደ ፊት ተገፍቶ ማክሰኞ ጥቅምት 13 11፡00 ላይ ይደረጋል። በሁለቱ የፍፃሜ ጨዋታዎች መካከል ያለው የሦስት ቀናት ልዩነትም ለሁለቱ ክለቦች በቂ የማገገሚያ ጊዜ ለመስጠት ታስቦ የተተወ እንደሆነ ታውቋል።