ከፍተኛ ሊግ | ገላን ከተማ አስር ተጫዋቾች ሲያስፈርም የአሰልጣኙን ውል አድሷል

በኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ሁለተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ወደ የከፍተኛ ሊግ ያደገው ገላን ከተማ 10 አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የአስራ አራት ነባር ተጫዋቾችን ውል አራዝሟል።

ምስረታውን የዛሬ አራት ዓመት አድርጎ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ከፍተኛ ሊግ መቀላቀል የቻለው እና በወጣት አሰልጣኝ እና በወጣት ተጫዋቾች የተዋቀረው ገላን ከተማ በከፍተኛ ሊግ ለሚኖረው የዘንድሮ ዓመት ተሳትፎ ራሱን በተሻለ ሁኔታ ለውድድሩ ብቁ አድርጎ ለማቅረብ በርካታ ማሻሻያዎችን እያደረገ ይገኛል። በአዳማ ከተማ ተስፋ ቡድን በነበረው የማሰልጠን ቆይታ በርካታ ታዳጊ ወጣት ተጫዋቾችን ለዋናው ቡድን በማሳደግ መልካም ስም ያተረፈው እና በአጭር ጊዜ የገላን ቆይታው ቡድኑን ወደ ከፍተኛ ሊግ ማሳደግ ያስቻለው ወጣቱ አሰልጣኝ ዳዊት ታደሰ ከክለቡ ጋር ለተጨማሪ ዓመት የሚያቆየውን ውል ሲያራዝም ባለፈው ዓመት ከቡድኑ ውስጥ ከነበሩ ነባር ተጫዋቾች መካከል 14 ተጫዋቾችን በክለቡ ማስቀጠል ችሏል።

በክለቡ ለተጨማሪ ዓመት የሚቆዩት ተጫዋቾች ውብሸት ጭላሎ ፣ ሰሚር ነስሩ ፣ አንተነህ መሰለ ፣ ማቲያስ ታደሰ ፣ አቡበከር ዓሊ ፣ አንተነህ ደርቤ ፣ ጅብሪል መሐመድ ፣ እሸቱ ጌታሁን ፣ አብዱላሒም ሙስጠፋ ፣ ዓለማየው ኃይሉ ፣ ያሬድ እሸቴ ፣ ታምራት ኃ/ማርያም እና ተሾመ መንግስቴ ናቸው። ከዚህ ውጪ የሚገኙ ተጫዋቾች ወደ ሌሎች ክለቦች ያመሩ እና የተቀነሱ ናቸው ።

ገላን በለቀቁት 10 ተጫዋቾች ምትክ አስር አዳዲስ ተጫዋቾች አስፈርሟል። የቀድሞው የብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ተመስገን ጮኖሬ (ከወልቂጤ)፣ ተላካዮቹ ሚኪያስ ዓለማየሁ (አማራ ውሃ ስራ) ፣ ማትያስ ድንቁ (ለገጣፎ) ፣ ወንድወሰን ቦጋለ (አዳማ) ፣ ዮናታን ዓባይ (ናኖ ሁርቡ) ፣ ቢንያም ዳንኤል (ነገሌ ቦረና) ፣ አማካዮቹ ዳግም አስቻለው (አክሱም) ፣ ብሩክ እንዳለ (አቃቂ ቃሊቲ) ፣ ምንተስኖት መንግስቱ (ነጌሌ ከተማ) እንዲሁም አጥቂው አጥቂ ዮሐንስ ደረጄ (መከላከያ) ክለቡን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ናቸው።

ውል ካራዘሙት መካከል እሸቱ እና አንተነህ

ከተለያዩ የተስፋ ቡድኖች ተጫዋቾችን በማስፈረም ለከፍተኛ ሊግ የበቃው ገላን ዘንድሮም በመከላከያ ከ17 ዓመት በታች እና ከ20 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ እንዲሁም በ2009 በዋናው ቡድን ማደግ ችሎ አምና በድጋሚ ከ20 ዓመት በታች ቡድን ተመልሶ የቡድኑ አምበል በመሆን ሲጫወት የቆየው ዮሀንስ ደረጄ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ያመራው የኋላሸት ፍቃዱን ክፍተት እንደሚሸፍን ይጠበቃል። የከፍተኛ ሊግ ልምድ ያላቸው ሚኪያስ እና ተመስገን አምና በወላይታ ድቻ ያሳለፈው ወንድወሰን ቦጋለ ስብስቡን እንደሚያጠናክሩም ይጠበቃል።

ገላን ከተማ በቅርቡ ተጨማሪ ተጫዋቾችን እንደሚያስፈርም ሲጠበቅ በህዳር ወር አጋማሽ ለሚጀመረው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በአዳማ ከተማ በማድረግ ላይ ይገኛል።