“ባሳዩኝ ክብር እና በሰጡኝ እውቅና ከፍተኛ የሆነ ደስታ ነው የተሰማኝ” መስዑድ መሐመድ

በ2002 ክረምት ኤሌክትሪክን በመልቀቅ ኢትዮጵያ ቡናን ከተቀላቀለ በኋላ በአጨዋወቱ እና በመልካም ባህርዩ በክለቡ ተወዳጅ ከሆኑ ተጫዋቾች አንዱ መሆን የቻለው መስዑድ በ2003 ቡና የሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ የቡድኑ አባል የነበረ ሲሆን ከ2007 ጀምሮም አምበል ሆኖ ያገለገለበትን ክለብ ለቆ ወደ ጅማ አባ ጅፋር ካመራ በኋላ በዛሬው ዕለት በተከናወነው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ሁለቱ ክለቦች ሲገናኙ ከቀድሞ ክለቡ አቀባበል ተደርጎለታል። 

ከጨዋታው ጅማሮ አስቀድሞ የኢትዮዽያ ቡና ደጋፊዎች ማኅበር እና አብረውት በቡና የተጫወቱ ተጨዋቾች መስዑድ በኢትዮዽያ ቡና በነበረው ቆይታ ለቡድኑ የሰጠውን የማይረሳ አገልግሎት ክብር እና እውቅና ለመስጠት አስገራሚ የሆነ የክብር አቀባበል አድርገውለታል። ይህ ሁኔታ የፈጠረበትን ስሜት አስመልክቶ ለሶከር ኢትዮጵያ ይህን ብሏል። ” በጣም ከባድ ስሜት ነው። በመጀመርያ ደጋፊዎቹን እና ተጫዋቾቹን ማመስገን እፈልጋለሁ። ባሳዩኝ ክብር እና በሰጡኝ እውቅና ከፍተኛ የሆነ ደስታ ነው የተሰማኝ፤ በጣም ነው የማመሰግነው።” ብሏል።

በክረምቱ የተቀላቀለበት ጅማ አባ ጅፋር በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ እየተሳለፈ ቢሆንም መስዑድ ግን ያደረገው ተሳትፎ እምብዛም ነው። ለዚህ ምክንያት የሆነውም ከግል ጉዳዮች እና መጠነኛ ጉዳት ጋር በተያያዘ በተሟላ ሁኔታ ልምምድ ባለማድረጉ እንደሆነ ገልጿል።  

ወደፊት ወደ ኢትዮጵያ ቡና ተመልሶ በተለያዩ መንገዶች ለማገልገል ስላለው እቅድ የተጠየቀው መስዑድ ” እንግዲህ የወደፊቱ ምን እንደሚፈጠር አይታወቅም። አሁን ላለሁበት ክለቤ ጅማ አባ ጅፋርን ያለኝን ነገር መስጠት እፈልጋለሁ። ወደፊት የሚሆነውን አብረን እናያለን። ” ሲል መልሷል። 

መስዑድ በመጨረሻም ዛሬ በቀድሞ ክለቡ የተሰጠው ክብርን በተመለከተ ለወጣት ተጫዋቾች የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፏል። “በመጀመርያ እግርኳስን መውደድ አለባቸው፤ ከወደዱት ሁሉ ነገር ይሆናል። በመቀጠል ልምምዳቸውን በሚገባ በመስራት እረፍታቸውን በአግባቡ መጠቀም ሲችሉ ትልቅ ቦታ መድረስ ይችላሉ ብዬ ነው ወጣቶችን መምከር የምፈልገው።”