ቅዱስ ጊዮርጊስ ሶስት የውጪ ዜጋዎችን አስፈረመ

በጥቂት ቀናት ውስጥ የሚዘጋው የውጪ ተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ክለቦቻችንን ጥድፊያ ውስጥ የከተታቸው ይመስላል። ባልተለመደ ሁኔታ የውጪ ተጫዋቾች ሳያስፈርም የውድድር ዘመኑን ለመጀመር ተቃርቦ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስም ሦስት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቋል።

ፓትሪክ ማታሲ የረጅም ጊዜ የፈረሰኞቹ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራን ተክቶ የቅዱስ ጊዮርጊስን በር የሚጠብቅ ይሆናል። ኬንያዊው ኢንተርናሽናል ባህር ዳር ላይ ከተከናወነው የኢትዮጵያ እና ኬንያ ጨዋታ በኋላ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለማምራት መስማማቱን በድረ-ገፃችን ማስነበባችን የሚታወስ ሲሆን ከክለቡ ተስካር መልቀቂያውን ከወሰደ በኋላ ለፈረሰኞቹ ፈርሟል።

ቶጓዊው ኢሲፎ ቦውራሀና ሌላው አዲስ ፈራሚ ነው። ከመፈረሙ በፊት የአንድ ወር የሙከራ ጊዜ በክለቡ ያሳለፈው የ26 ዓመቱ የቶጎ ብሔራዊ ቡድን እና የቀድሞ ቶጎ ፖርት ተጫዋች ቦውራሀና የቀኝ መስመር ተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ሲሆን በመሐል ተከላካይነትም መጫወት ይችላል።

እንደ ቦውራሀና ሁሉ በክለቡ የሙከራ ጊዜ አሳልፎ የነበረው ካሲሙ ግሎቨር ሶስተኛው ፈራሚ ሆኗል። የ23 ዓመቱ አማካይ በሀገሩ ክለቦች አሚደስ ፕሮፌሽናልስ እንዲሁም በጋቦኖቹ ፔሊካን እና ሲኤፍ ሞናና ተጫውቷል።