የከፍተኛ ሊግ ዕጣ ማውጣት ስነ-ስርዓት የሚደረግበት ቀን ተሸጋሽጓል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ አዲሱ የውድድር ዓመት እጣ ማውጣት ስነ ስርዓት እና ያለፈው ዓመት አፈፃፀም  ሪፖርት የሚቀርብበት ቀን ላይ መሸጋሸግ ተደርጎበታል።

ኅዳር 15 እንደሚጀመር የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የዕጣ ማውጣት ስነ-ስርዓት ጥቅምት 15 እንደሚደረግ መርሐ ግብር ተይዞለት የነበረ ቢሆንም በሴቶች ፕሪምየር ሊግ ስብሰባ ምክንያት ወደ ፊት ተገፍቶ ጥቅምት 20 በኢትዮጵያ ሆቴል እንደሚደረግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለሶከር ኢትዮጵያ አስታውቋል፡፡ በዕለቱ 2010 አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2011 የውድድር ዘመን ዕጣ የማውጣት ስነ-ስርዓት እንዲሁም የውድድር ደንብ ላይ ውይይት የሚደረግ ይሆናል። የከፍተኛ ሊጉ ውድድር ከ2008 ጀምሮ በሁለት ምድብ ተከፍሎ ሲደረግ የቆየ ሲሆን ዘንድሮ እንዳለፉት ዓመታት በተመሳሳይ በሁለት ምድቦች ተከፍሎ ይደረግ ወይስ የተለየ የውድድር አካሄድን ይከተል የሚለው አጀንዳ ይነሳበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ኅዳር 1 እንደሚጀመር የተገለፀው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን እና ሁለተኛ ዲቪዝዮን ውድድሮች የዕጣ ማውጣት እንዲሁም የደንብ ውይይት ለከፍተኛ ሊግ በተቆረጠለት ቀን (ጥቅምት 15) ይከናወናል። ያለፈው የውድድር ዓመት አፈፃፀም ሪፖርትም በዕለቱ የሚቀርብ ይሆናል።