ቅዱስ ጊዮርጊስ አራተኛ የውጪ ዜጋ ዝውውርን አጠናቀቀ

በትላንትናው ዕለት የኬንያ፣ ቶጎ እና ጋና ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾችን ያስፈረመው ቅዱስ ጊዮርጊስ በዛሬው ዕለት ደግሞ ናይጄርያዊ አጥቂ በእጁ አስገብቷል፡፡

አሌክስ ኦሮቶማ የሩዋንዳው ሰንራይዝ ክለብን በመልቀቅ ወደ ኬንያው ክለብ ኤፍሲ ሊዮፓርድስ የተዛወረው ጁላይ 2018 (በኬንያ የውድድር ዘመን አጋማሽ ዝውውር መስኮት) ላይ ለሁለት ዓመት በሚቆይ ውል ቢሆንም ከ3 ወራት ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ፊርማውን አኑሯል፡፡

ባለፈው ዓመት በጉዳት ሳስቶ የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ የአጥቂ መስመር በሶስት አደዲስ ፈራሚዎች ተጠናክሯል፡፡ ከአሌክስ በተጨማሪ ጌታነህ ከበደ እና አቤል ያለውን ያስፈረመው ክለቡ ከጉዳቱ የተመለሰው ሳላዲን ሰዒድ እና አሜ መሐመድን በስብስቡ ይዟል፡፡