ሶከር መፅሀፍት | ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ (ምዕራፍ አንድ- ክፍል ሁለት)

በዝነኛው እንግሊዛዊ የእግርኳስ ፀኃፊ ጆናታን ዊልሰን የተደረሰውና በእግርኳስ ታክቲክ ዝግመታዊ የሒደት ለውጦች ላይ የሚያተኩረው Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የተሰኘውን መጽሃፍ በትርጉም እያቀረብንላችሁ እንገኛለን። በዛሬው መሰናዶም የምዕራፍ አንድ ሁለተኛ ክፍልን እነሆ ብለናል፡፡ መልካም ንባብ!


|| የመፅሀፉን ክፍል አንድ ለማንበብ ይህን ይጫኑ – (ምዕራፍ አንድ- ክፍል አንድ)


ከአስራ አራት ዓመታት በኋላ በደቡባዊው የሃገሪቱ ክፍል እግርኳስን በሚመለከት በህዝቡ ዘንድ የነበረው አተያይ በየጊዜው የማይለዋወጥና መደበኛ የመሆን ባህሪ በማሳየት ረገድ አንድ ደረጃ ከፍ አለ፡፡ የአፒንግሀም ት/ቤት ርዕሰ መምህር የነበረው ኤድዋር ትሪንግ ታናሽ ወንድም ጄ.ሲ.ትሪንግ በካምብሪጅ የጨዋታ ደንብና መመሪያዎችን የማርቀቅ ቀዳሚ ሙከራዎችን ሲያሰናክል ወይም ሲቃወም እንዳልነበር ሁሉ አስር ህግጋትን የያዘና ቀላሉ ጨዋታ የተሰኘ ሰነድ አዘጋጀ፡፡ በዚያው ዓመት መስከረም ወር ላይ የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የእግር ኳስ ህግጋት የሚል ሌላ መመሪያም ለህትመት በቃ፡፡ ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ ወሳኙ የእግር ኳስ ማኅበር ተቋቋመ፡፡ ወዲያውኑም መደበኛና ዘላቂ የድሪብሊንግና ኳስ አያያዝ የተመረጡ ባህርያትን ለመቀላቀል የሚያስችል የእግር ኳስ መተዳደሪያ ደንብና መመሪያዎችን ለማውጣት ተሞከረ፡፡ ሆኖም የጨዋታ ህግጋቱን የማዋሃድ ጥረት ሳይሳካ ቀረ፡፡ ክርክሩ ከባድና ረዘም ያለ ጊዜም ወሰደ፡፡

ታህሳስ 8 ቀን 1863 ልክ ከምሽቱ 1:00 ሲል ለንደን በሚገኘው ትልቁ የሊንኮን አደባባይ በፍሪማሰን ታቭረን መናፈሻ ለአምስተኛ ጊዜ በተካሄደው ጉባዔ ኳስን በእጅ መያዝ ከህግ ውጪ ሆነ፡፡ በዚህም እግርኳስና ራግቢ የሚለያዩባቸው መንገዶች ግልጽ ተደረጉ፡፡ ባልተለመደ መልኩ አለመግባባት ላይ የተደረሰው በጨዋታው ወቅት እጅን ከመጠቀም ጋር በተያያዘ ጉዳይ አልነበረም፤ ይልቁንም የባላጋራ ቡድን ተጫዋቾችን በቁርጭምጭሚትና በጉልበት መካከል የሚገኘው የእግር ክፍል ላይ መገጫጨትን ከመፍቀድ ጋር በተገናኘ ነበር፡፡ የብላክሂዙ ተወካይ ኤፍ. ካምቤል ጠንካራውን አካላዊ ንክኪ የመደገፍ አዝማሚያ አሳየ፡፡ ” መማታትን የምትከለክሉ ከሆነ በዚያው ልክ ከጨዋታው ብርታትና ድፍረትን ታጠፋላችሁ፡፡ እኔም በአንድ ሳምንት ልምምድ ብቻ የሚረቱዋችሁን በርካታ ፈረንሳውያን ለማምጣት እገደዳለሁ፡፡” አላቸው፡፡ በእርሱ አረዳድ ስፖርት ህመምን የመቻል ጽናት፣ ጭካኔና ጀብደኝነት የሚፈልግ ነው፡፡ “በተፈጥሯዊ ክህሎት ላይ ብቻ ተመሰርተን ድልን ካሰብን ምናልባት ማንኛውም የሌላ ሀገር በእድሜ የገፋ ሰውም አሸናፊ የመሆን እድል ሊኖረው ይችላል፡፡” ሲልም አፌዘባቸው፡፡ ሀሳቡ የቀልድ ይዘት ያለው ቢመስልም የክርክሩ ዐብይ ጉዳይ አጠቃላይ የእግርኳስ አጨዋወት ላይ ያለ እምነትን ወይም ባህልን የሚወክል ነበር፡፡ ውሎ እያደር ሆን ተብሎ መማታትን የመሳሰሉ አደገኛ አጨዋወቶች ሙሉ በሙሉ ሲከለከሉ ብላክሂዞች ከእግር ኳስ ማህበሩ ራሳቸውን በገዛ ፈቃዳቸው አገለሉ፡፡

ከጨዋታ ውጪ> ደንብ ቀደም ብሎ የመጣው የ<ስድስተኛው ህግ> በሒደት የድሪብሊንግ ስልትን እየተስፋፋ እንዲሄድ ረዳ፡፡ ደንቡ ”አንድ ተጫዋች ኳሱን ወደፊት ሲመታ ለተጋጣሚ ቡድን የግብ ክልል የተጠጋ የትኛውም የኳስ መቺው ወገን ተጫዋች ከጨዋታ ውጪ ይሆናል፡፡ የጨዋታው አካል እስኪሆን ድረስም ኳሱን መንካት አይችልም፡፡ በማንኛውም መንገድ ሌሎች ተጫዋቾች እንዳይጫወቱ መከላከልም አይችልም፡፡” ይላል፡፡ በሌላ አገላለፅ በዚህ የጨዋታ መመሪያ መሰረት ቅብብሎች በብዛት መከናወን የሚኖርባቸው የጎንዮሽ አልያም ወደ ኋላ ነበር፡፡ በቀጥታ የአካላዊ ንክኪን ተገን ያደረገ ጨዋታ ዋነኛ የአጨዋወት ባህሪ አድርጎ ለወሰደና ላመነ አንድ እንግሊዛዊ ሰው ሌላ አካሄድን መሞከር ብልጣብልጥነትና ፈሪነትን የማሳየት መንገድ ነው፡፡ እውነታው ግን መቼም ያን ሆኖ አያውቅም፡፡

በጊዜው ይታይ የነበረው ድሪብሊንግ በራሱ ከዘመናዊው እግርኳሳዊ ጥበብ አረዳድ ጋር የተለያየ ነበረ፡፡ የኤፍ.ኤ.ዋንጫ ውድድር ታሪክን በሚያወሳው መጽሀፉ የቀድሞ የዘ-ሰን እግርኳስ ዘጋቢ ጂኦፍሬይ ግሪን በ1870ዎቹ የነበረና ስሙ ያልሰፈረ ጸኃፊን ጠቅሶ ” በትክክልም ጥሩ ክህሎት ያለው ተጫዋች የኳሷን አቅጣጫ ሳይስት፤ በተመሳሳይ ሰዓት ደግሞ ትኩረቱን በባላጋራ ቡድን ክፍተቶች ላይ በማሳረፍ፤ ዕይታውን የተጋጣሚ ቡድን የመከላከል ደካማ ጎኖች ላይ በማድረግ ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ ወዳሰበው ተቃራኒ ቡድን ክልል የሚያደርሰውን እድል ያመቻቻል፡፡

አልፎ አልፎ በጣት የሚቆጠሩ ተጫዋቾች ኳሷን በእግሮቻቸው መሀል ክብ ሰርተው ሲያንከባልሉና ሲገፉ ማየት፣ ሁኔታዎች ሲፈቅዱ ደግሞ ኳሷን እንደያዙ አቅጣጫ ሲቀይሩ መመልከት ሊረሳ የማይችል ትውስታ ነው፡፡ በድሪብሊንግ ላይ የሚታየው ክህሎት ያለፍርሀት በቀጥታ ወደ ተጋጣሚ ቡድን ከመስፈንጠርና በጭፍን ወይም ያለምንም ማወላወል የጠላት ምሽግ ላይ ድንገተኛ ጥቃትን ከመፈጸምም በላይ የተጋጣሚ ቡድን ደካማ ጎኖችን የሚያማትር ዓይን እንዲሁም ወደ ባላጋራ ክልል ለመድረስ የሚያስችል ስኬታማ መንገድ የሚያስገኝ ቀመር ማወቅና በሱ ላይ ውሳኔ መስጠትን የሚጠይቅ ተፈጥሯዊ ብልጠት ይፈልጋል፡፡” በማለት ጠቅሷል፡፡ የዚያን ጊዜውን እግርኳስ ሜዳ ላይ ከሚታየው የተጫዋቾች ቦታ አያያዝ ቅርጽ አንጻር ስንመለከተው ኳስን በእጅ ከመያዝ ውጪ ዘመነኛውን የጀማሪዎች ራግቢ ጨዋታን ይመስል ነበር፡፡

በእርግጥ ለጊዜው እግርኳስ እጅጉን የገዘፈ ጉዳይ ባይሆን እንኳ የተጫዋቾች ቁጥር አስራ አንድ እንዲሆን ከተወሰነ በኋላ ታክቲክ መሰረታዊ ዋጋ ነበረው፡፡ ያኔ ቡድኖች በዘፈቀደ ኳሷን የማባረር ልማድ አሳይተዋል፡፡ እስከ 1870ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት ድረስ የግብ ጠባቂነት ቦታ በሁሉም የእግርኳሱ አካላት ዘንድ ተቀባይነት ያገኘና እውቅና የተሰጠው ሚና አልነበረም፡፡ ከቀሪ የቡድን ተጫዋቾች የተለየ መለያን የመልበስ ልማድ የመጣውም በ1909 ነበር፡፡ እስከ 1912 ድረስ ደግሞ አንድ ግብ ጠባቂ በራሱ የመጫወቻ ሳጥን ክልል ውስጥ ብቻ ኳስን በእጁ እንዳይዝ አልተከለከለም፡፡ የህግ ለውጡ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው የጊዜው የሰንደርላንድ ግብ ጠባቂ ሌይ ሪችሞንድ ሮዝ የሜዳው ቁመት አጋማሽ ድረስ እየወጣ ኳስ በእጁ የሚይዝበትን ባህሪ ለማረቅ ሲባል ነበር፡፡ በእነዚያ ቀደምት ዘመናት በፎርሜሽኖች ደረጃ የሚጠቀስ ነገር ቢኖር ሁለት ወይም ሶስት የኋላ መስመር ተሰላፊዎች እና ዘጠኝ አልያም ስምንት የፊት መስመር ተጫዋቾችን ማየት ሊሆን ይችላል፡፡

በኤተኑ ጉባዔ የጸደቀውና ” ልክ ኳሱ ሲመታ ቢያንስ ሶስት የሚከላከለው ቡድን ተጫዋቾች በራሳቸው የጎል ክልል እና በአጥቂው ቡድን ተጫዋች መካከል ከተገኙ የፊት ለፊት ረጃጅም ቅብብሎች ይፈቀዳሉ፡፡” ( በዚህ ጊዜ ተግባራዊ እየተደረገ ካለው ደንብ በአንድ ተጫዋች የበለጠ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡) የሚለው ስድስተኛው ሕግ በ1866 ሲለወጥ የድሪብሊንግ አጨዋወትን ለሚመርጡት ሰዎች የተሻለ ልዩነት ይዞ ብቅ ያለ ውሳኔ ሆነ፡፡

ከቀደምት ተጫዋቾች የሚመደበውና በ1870ዎቹ መጨረሻ በአስተዳደር ስራ ላይ የተሰማራው ቻርለስ አልኮክ ኳስን ወደ ኋላ የመመለስ፣ የማቀበልና የመደጋገፍ ዋነኛና ጠቃሚ መርሆዎች> የተሰኘው መመሪያው ላይ ” የቡድን አጋርን መደገፍ ስል በቅርብ ርቀት እየተከታተልኩት እርሱን ማገዝ፣ ሲያስፈልግም ሊጠቃ ወይም ኳሱን ሊቀማ ሲል አልያም ጫና ሲደርስበት ኳሱን ልቀበለው እና በቦታው የሚገጥመውን ፈተና ልከላከልለት ይገባል ማለቴ እንደሆነ ታሳቢ ይደረግልኝ፡፡” በማለት የመጫወቻ ደንቦችን በአዲስ መልክ ያዘጋጅ ነበር፡፡ የእግር ኳስ ማኅበሩ ከተመሰረተ ከአስር ዓመታት በኋላ ጨዋታውን በማስፋፋት የአንበሳውን ድርሻ ከሚወስዱት የቀድሞ ሰዎች አንዱ የሆነው አልኮክ በጨዋታ መሀል አንድ የቡድን አጋሩ በጎል አካባቢ ኳስን በግንባሩ ወደ ታች ሲያወርድ ወደ እርሱ ሮጦ በመሄድ ማገዝ ወይም መርዳት በጣም ጥሩ ሀሳብ ሲሆን ያንኑ ኳስ በፈቃደኝነት ለመቀበል መፈለግ ደግሞ የተሻለ አስተዋጽኦ ለማበርከት መነሳሳትን የማሳየት እንቅስቃሴ እንደሆነ ለሌሎች ማብራራት አስፈላጊ መሆኑ ተሰማው፡፡

ይህ መሰሉ አካሄድ እንግዲህ በደቡቡ የሀገሪቱ ክፍል የነበረው ሲሆን የሰሜኑ ክፍልም የራሱን መጠነኛ እመርታ ያሳይ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ በደቡብ ዮርክሻየር ግዛት በሼፊልድ ኮሌጅ የነበሩ የኦልድ ሃሮቪያን መምህራን እና የሆልሚፈርዝና ፔኒስተን> ሀገርኛና ባህላዊ ጨዋታዎች መዋሃድ በጥቅምት 1857 የሼፊልድ ክለብ እንዲመሰረት አስቻለ፡፡ ክለቡ ሲቋቋም የመጀመሪያ አላማው የክሪኬት ተጫዋቾች በክረምት ወቅት የአካል ብቃታቸውን ጠብቀው እንዲቆዩ ለማገዝ ተብሎ ነበር፡፡ በዚያ ዓመት የቦክሲንግ ዴይ ክብረ በዓል ላይ በዓለም የመጀመሪያው በክለቦች መካከል የተካሄደ ግጥሚያ ተደረገና ሼፊልዶች ሃላም እግርኳስ ክለብን 2-0 ረቱ፡፡ እግርኳሱም በፍጥነት ማደጉን ቀጥሎ በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በርካታ ተከታታዮችን መሳብ ቻለ፡፡ በአካባቢውም ወደ 15 የሚጠጉ ክለቦች ተመሰረቱ፡፡ ሼፊልድ ክለብም የሀሮው፣ ራግቢና ዊንቼስተር ቡድኖች ተጽዕኖን የሚያሳይ እንዲሁም ከጨዋታ ውጭ መመሪያ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሌለው የራሱን ህግና ደንብ አርቅቆ በ1862 ለህትመት አበቃ፡፡

እንዲያም ሆኖ በጨዋታዎች ወቅት መጠነኛ ደንቦች ሲተገበሩ ይታይ ነበር፡፡ የጊዜው የሼፊልድ ክለብ ዋና ጸኃፊ ዊሊያም ቼስተርማን አዲስ ለተቋቋመው የእግር ኳስ ማህበር በኅዳር 30-1863 ባቀረበው ጽሁፍ ክለቡ በተወሰነ ጊዜ ለማኅበሩ የሚከፍለውን ገንዘብ እንዲሁም በህግና መመሪያዎች አማካኝነት በሚነሱ ክርክሮች ላይ ስለሚያደርገው አበርክቶ  ” በአጠቃላይ የእናንተን ስድስተኛው ህግ መሰል የታተመ ደንብ ባይኖረንም በመጽሐፌ ውስጥ ዘወትር ስንጫወት የምንጠቀምበትን ህግ ጽፌያለሁ፡፡” በማለት ቢጠቅስም የተናገረው በትክክል ግልጽ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ ቆይቷል፡፡ የሼፊልድ ከጨዋታ ውጭ ህግ መደበኛ ተቀባይነት ያገኘው በ1865 ነው፡፡ ሼፊልዶች ከኖትስ ካውንቲ ጋር ከመጫወታቸው ቀደም ብሎ የጨዋታ ህጎችን ከመለዋወጥና ከመጋራት ስምምነት አኳያ በወቅቱ አንድ አጥቂ በጨዋታ እንቅስቃሴ ውስጥ> እንዲሆን በራሱ የግብ ክልል ከሚከላከለው ቡድን አንድ ተጫዋች ብቻ እንዲገኝ ያስፈልግ ነበር፡፡ በእርግጥ በቅብብሎች የሚፈጠሩ እድሎች ጥቅም ላይ የሚውሉበት መጠን አከራካሪ ቢሆንም ሒደቱ ግን እድገታቸውን ይበልጥ ያበረታታ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የእግርኳስ ማህበሩ የሼፊልድን ቅድመ ሁኔታ መስፈርት ሳይቀበል ቀረ፡፡ በዚህም ምክንያት ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ህጎች በኖቲንግሐምና በሀገሪቱ በሚገኙ ሌሎች ከተሞች በጥቅም ላይ ሲውሉ ከረሙ፡፡ በየካቲት 30/1866 ለመጀመሪያ ጊዜ በባተር ሲ ፓርክ ለንደንና ሼፊልድ በሚያደርጉት ጨዋታ ላይ ክለቦቹ ተገናኙና ለንደኖቹ የ2-0 ድል ቀናቸው፡፡ የወቅቱ ዘገባዎች ለንደኖቹ የተሻለ ክህሎት ቢያሳዩም በሼፊልዶች አካላዊ ፍልሚያ ላይ ያመዘነ አቀራረብ እንዳልተረጋጉ ያስረዳሉ፡፡

በየትኛው የእግርኳስ ህግ መጫወት እንደሚሻል ለተደጋጋሚ ጊዜ ከታሰበበት በኋላ በታህሳስ 1871 አልኮክ የለንደን ቡድንን ይዞ ወደ ሼፊልድ ብቅ አለ፡፡ በሼፊልዶች የጨዋታ ህግ መሰረት በተከናወነው ግጥሚያ ባለሜዳዎቹ የ3-1 ድል ተቀዳጁ፡፡ የአሸናፊነታቸው ምስጢር ተጫዋቾች በሜዳ ላይ ያሳዩት የተደራጀ አቋቋምና የተጠናከረ ቅርጽ እንደነበር የሚያመለክቱ አመክንዮዎች ይንጸባረቁ ጀመር፡፡ ይህ ጠንካራ ጎናቸው ‘ይበልጡን የተሻለ ነጻነት አለው፡፡’ ተብሎ ከሚታሰበው የጨዋታ ውጭ ህጋቸው ጋር ተዳምሮ የቅብብሎች ጨዋታን የተሻለ ግምት አሰጠው፡፡ ሆኖም ሼፊልዶች ከለንደኖቹም በተሻለ የድሪብሊንግ አጨዋወትን የተካኑበት ይመስሉ ነበር፡፡ ፔርሲ ያንግ በፉትቦል ኢን ሼፊልድ ላይ ያቀረበው ጽሁፍም “የክለቡ ተጫዋቾች አልኮክ ይዞት የመጣው የድሪብሊንግ ክህሎት ከእነርሱ ልምድ አንጻር እጅጉን የተለየ ሆኖ አግኝተውታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ  አልኮክ ልኬቱንና የኳሱን ትክክለኛ መዳረሻ የጠበቀ ቅብብል የመከወን ጸጋን የታደለ ነበር፡፡ በቁጥር ወደ ሁለት ሺህ ለሚደርሱት ኳስ ተመልካቾች በአልኮክና በቼነሪ መካከል የታየው የተሳካ ጥምረትም አስገራሚና አስደሳች ነበር፡፡(በወቅቱ የተወሰኑ የከተማው ተጫዋቾች ከገዛ ጓደኞቻቸው የሚደርሳቸውን እና በእያንዳንዱ አጋጣሚ የሚያገኙትን ኳስ በቀጥታ ወደፊት መምታት ትተው ቀለል ያለና ይበልጥ ቀጥተኛ የሆነ የአጨዋወት ዘዴን ተቀበሉ፡፡)” ሲል ያስረዳል፡፡ 1878 ላይ ሼፊልዶች የእግርኳስ ማህበሩ አባል ከመሆናቸው በፊት አስራ ስምንት የማግባቢያና ድርድር ስብሰባዎችን መጥራት አስፈልጓል፡፡

በሼፊልድ ቅብብሎች ላይ የተመሰረተ የአጨዋወት ባህል የተለመደ አልነበረም፡፡ የመጫወቻ መስመራቸው ወይም አካባቢያቸው ላይ የሚኖር ጥቃትን ለማስወገድ ኳሱን በረጅሙ የሚለጉት ይመስሉ ነበር፡፡ ጂኦፍሬይ ግሪን ዘ ወርልድ ጌም መጽሃፍ ላይ የሼፊልድ ተጫዋቾች የኤግዚብሽን ጨዋታ ለማድረግ በ1875 ለንደን ሲደርሱ “ኳስን በግንባር መግጨት ጀመሩ፤  ተመልካቾችም ድርጊቱን ከማድነቅ ይልቅ በመዝናኛነት ስሜት ተመለከቱት፡፡” ሲል አውስቷል፡፡ በንጹህ የድሪብሊንግ ጨዋታ አካሄድ ኳስ የማንከባለሉን ሒደት ለማጨናገፍ አልፎአልፎ ከተጋጣሚው እግር በላይ ለማንሳት ከሚደረገው ጥረት ውጪ ኳሱ የሜዳውን ወለል የሚለቅበት ሁኔታ የግድ መኖር የለበትም፡፡ በንጹሁ የዚህ አጨዋወት ስልት በአየር ላይ በአንጻራዊ ከፍታ የሚገኝን ኳስ ለመጫወት ብቻ  በግንባር መግጨት አስፈላጊ ይሆናል፡፡

በግላስኮውና በሼፊልድ መካከል የተደረገውን ጨዋታ ዘገባ የሚያሳየው የ1877ቱ የስኮትላንድ እግር ኳስ ማኅበር ዓመታዊ ሪፖርት ሀሳቡን በአግባቡ የመግለጽ አቅም አለው፡፡ ”ጨዋታው እጅጉን ጥሩና ደማቅ ፉክክር የታየበት፣ ማንንም የሚያስማማው ምርጡ ቡድን ድል የተቀዳጀበት እና ማራኪ ነበር ፡፡ ጥቂቶች ብቻ የሚቀበሉት ቢሆንም ከሌሎች በተለየ የስኮትላንድ ቡድኖች ውስጥ የተትረፈረፈ በድሪብሊንግ ስልት የመጫወት ውህደት የመኖሩ እውነታ ሊደበቅ የሚችል አይደለም፡፡ በቅዳሜው ጨዋታ የሼፊልድ ቡድን የተከተለው ታክቲካዊ አቀራረብ የቻሉትን ያህል ከእንግሊዝና ስኮትላንድ እግርኳስ ማኅበራት ተነጥለው በሌላ የጨዋታ መመሪያ ለመጫወት ከመወሰናቸው ጉዳይ ጋር ሰፊ ተዛማጅነት ይኖረዋል፡፡ የጨዋታ ውጭ ደንባችን ለእነርሱ ጉዳያቸውም አልነበረም፡፡ በዚህ ሁኔታ በረጅሙ ኳስን ወደፊት መለጋት በዚያ ዕለት ብልጫ ተወሰደበት፡፡ ተመሳሳይ የአጨዋወት ስልት ለመተግበርም የግላስኮው ቡድን በትልልቅና ከባባድ ፍልሚያዎች ድል ያስገኘለትን የህብረት ጥንካሬ አሳጣው፡፡”

በቅብብሎች እና በተጫዋቾች የኅብረት እንቅስቃሴ ላይ ለተመሰረተው ጨዋታ መስፋፋት ቀደም ሲል በ1872 በግላስኮው ሃምደን ፓርክ የተካሄደውን ጨዋታ መለስ ብለን መቃኘት ይኖርብናል፡፡ በዓለም የመጀመሪያ በሆነው የሃገራት እግርኳሳዊ ግጥሚያ ስኮትላንድ በሜዳዋ እንግሊዝን አስተናገደች፡፡ የእንግሊዛውያኑ አሰላለፍ ላይ ግብ ጠባቂ፣ ሶስት ተከላካዮች፣ በግርድፉ መሀል ላይ በሚል ብቻ የተገለጹ አራት ተጫዋቾች (ከእነዚህ ውስጥ ሃልፍ ባክ እና ፍላይ ኪክ የተባሉ የሜዳ ላይ ሚናዎች ነበሩ፡፡) እንዲሁም ሁለት በግራ መስመር የሚሰለፉና ሌላ አንድ ደግሞ በቀኝ መስመር የሚጫወት ተጫዋቾችን ያካተተ ሲሆን  በዘመነኛው ምስላዊ ገለጻ ጠመም ወደሚል የ1-2-7 ፎርሜሽን የተጠጋ ቅርጽን ያመለክታል፡፡ ”የቡድኑ ፎርሜሽን ሰባት የፊት መስመር ተጫዋቾችን የሚያቀርብና በሶስት የመከላከል አግድሞሽ መስመሮች ላይ አራት ተጫዋቾችን ብቻ የሚያሳትፍ ነበር፡፡ በእርግጥ በመጨረሻው የመከላከል መስመር የተጋጣሚ አጥቂዎችን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠረው ግብ ጠባቂው ሲሆን ከፊቱ አንድ የመስመር ተከላካይ ተገኝቶ ሁለት የተጋጣሚ የፊት መስመር ተሰላፊዎችን መጋፈጥ ይጠበቅበታል፡፡’ ሲል አልኮክ አክሏል፡፡

ስኮትላንዶቹ በሌሎች ጨዋታዎች ማለትም በክሪኬት ኤም.ሲ.ሲ፣ በጎልፍ  ደግሞ እና ሮያል የተሰኙት  ክለቦች እንደሚያደርጉት ሁሉ እግርኳስ ማህበራቸውን በ1873 ከመመስረታቸው በፊት የስፖርቱን ዘርፍ የሚያስዳድርላቸው ክዊንስ ፓርክ ክለብ ነበር፡፡  በመሰረቱ ከሰውነት ክብደታቸው አንጻር ስኮትላንዳውያን ከእንግሊዞቹ ቀለል ያሉ ነበሩ፡፡  ይህም በቀደመው ዘመን እግርኳስ ላይ የተክለሰውነት ጉዳይ ትልቅ ትኩረት እንደሚቸረው ዋነኛ ማሳያ ይሆናል፡፡ አብዛኛዎቹ የእግርኳስ ተንታኞችም ይህ የተጫዋቾች አካላዊ ግዝፈት እንግሊዝን ለታላቅ ድል ያበቃታል ብለው እንዲጠብቁ አድርጓቸዋል፡፡ በትክክል የሆነው ግን ተጨባጭ ለውጥ ያላሳየው ምናባዊ ሐሳብ ላይ ጊዜ ማባከን ብቻ ነው፡፡ ቀጥተኛ ማረጋገጫዎቹ ጥራዝ ነጠቅነት ቢያመዝንባቸውም የስኮትላንድ እግርኳስ ቤተመዘክር ሰራተኛው ሪቻርድ ማክብሬቲ እንደሚለው ኩዊንስ ፓርኮች ቀጥተኛ በሆነ አቀራረብ እና በወቅቱ ተጫዋቾች ከነበራቸው ግዙፍ ተክለሰውነት አኳያ ከፍተኛ ብልጫ የሚያስወሰድባቸውን የአንድ-ለ-አንድ ፍልሚያ ከመምረጥ ይልቅ ኳሱን በእንግሊዛውያኑ ተጫዋቾች ዙሪያ ለመቀባበል መወሰን ግድ ሆነባቸው፡፡ ፎርሜሽናቸው በእርግጥም የ2-2-6 ይዘት ነበረው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በግጥሚያው የታዩት ማዘናጊያ ድርጊቶችና ማብሸቂያ ቃላት ውጤቱ ላይ የራሳቸውን ተጽዕኖ አሳረፉ፡፡ በጥሩ ሁኔታ የተደራጀውና በርካታ የተጫዋቾች አማራጭ የነበረው የእንግሊዝ ቡድን ቅድመ ግምቱን ቢወስድም ጨዋታው ግን ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ፡፡ በግላስኮው ሄራልድ ላይ የወጣ ዘገባም ” እንግሊዞች በተጫዋቾች አካላዊ ቁመና ረገድ የተሻለ ተጠቃሚ የመሆን እድል ነበራቸው፡፡ የተጫዋቾቻቸው አማካይ ክብደት የስኮትላንዶቹን ተጫዋቾች ሁለት እጥፍ ይሆናል(ግነት የታከለበት)፤ በፍጥነት ረገድም የተሻሉ ነበሩ፤ የከተማው ክለብ ጠንካራ ጎን ደግሞ በሚያስገርም ልህቀት በህብረት መጫወታቸው ነበር፡፡” ብሏል፡፡


ይቀጥላል…


ስለ ደራሲው 

ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡  ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም የሚከተሉትን ዘጠኝ መጻህፍት ለህትመት አብቅቷል፡፡

-Behind The Curtain: Travels in Eastern European Football (2006)

-Sunderland: A Club Transformed (2007)

-Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics (2008)

-The Anatomy of England (2010)

-Brian Clough: Nobody Ever Says Thank You: The Biography (2011)

-The Outsider: A History of the Goalkeeper (2012)

-The Anatomy of Liverpool (2013)

-Angels With Dirty Faces: The Footballing History of Argentina (2016)

-The Barcelona Legacy: Guardiola, Mourinho and the Fight For Football’s Soul (2018)