መቐለ እና ወልዋሎ ሁለት ዓላማ ያለው የወዳጅነት ጨዋታ አዘጋጁ

ሁለቱ  ትግራይ ክልል ክለቦች በደጋፊዎቻቸው መካከል የተፈጠረው መቃቃር  በዘላቂነት ለመፍታት እና ከጨዋታው የሚገኘው ገቢም በክልሉ በተለያዩ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል ጨዋታ አዘጋጁ።

በክልሉ የወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ እንዲሁም በሁለቱ ክለቦች በጣምራ የተዘጋጀው ይህ ጨዋታ የደጋፊዎች እና የቡድኖቹን ጨዋታ ያጠቃለለ ሲሆን ገቢውም ለበጎ ዓላማ ለማዋል እንደታሰበ የጨዋታው አዘጋጆች ገልፀዋል። ጨዋታውም እሁድ ጥቅምት 12 በ7 ሰዓት እንደሚጀምር ታውቋል። ጨዋታው የተዘጋጀበት ዋና ዓላማ በተለያየ ምክንያት የተፈናቀሉት ወገኖች ለመርዳት ቢሆንም ከዋናው ዓላማ ጎን ለ ጎን  ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሁለቱም ክለብ ደጋፊዎች የሚታየው ተደጋጋሚ ግጭት  በዘላቂነት ለመፍታት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በማህበራዊ ጉዳዮች የሚበረታታ እንቅስቃሴ እያደረጉ የሚገኙት የኢትዮጵያ ክለቦች ከዚህ ቀደም የአማራ ክልል ክለቦች እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በጣና ሃይቅ ላይ የበቀለው እምቦጭ አረምን ለማጥፋት ያለመ ውድድር አዘጋጅተው እንደነበር ይታወሳል። በተጨማሪም የበርካታ ክለቦች ደጋፊዎች በተናጠል የትምህርት መሳሪዎች ያልተማሉላቸው ወገኖች በመደገፍ እና ደም በመለገስ ተመሳሳይ የበጎ ስራዎች ላይ መሳተፋቸው ይታወሳል።