ሽመልስ በቀለ ጎል ማስቆጠሩን ቀጥሎበታል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አማካይ ሽመልስ በቀለ በግብፅ ማንፀባረቁን በመቀጠል የሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን በመምራት ላይ ይገኛል።

በግብፅ ሊግ 11ኛ ሳምንት ቅዳሜ ማምሻውን በተካሄደ አንድ ጨዋታ ፔትሮጀት ከሜዳው ውጭ ከኢትሀድ አሌሳንድርያ ጋር 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል። ኢትሀድ ሪይ ካሲኢ በ27ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ጎል ቀዳሚ መሆን ቢችልም ሽመልስ በቀለ በ62ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠረው ጎል ፔትሮጀትን ነጥብ ተጋርቶ እንዲወጣ አስችሏል። በዚህም ክለቡ የወራጅ ቀጠና ውስጥ ቢገኝም በ7 ጎሎች የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቱን በመምራት ላይ ይገኛል። 

ከፔትሮጀት ጋር የውል ዘመኑ መጠናቀቂያ ዓመት ላይ የሚገኘው ሽመልስ ከባለፉት አራት ዓመታት በተሻለ ሁኔታ ዘንድሮ የቡድኑ አምበል ከመሆኑም ባሻገር መልካም የሚባል የውድድር ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል። ምንም እንኳን ክለቡ ፔትሮጀት እንደ ቡድን ውጤታማ መሆን ባይችልም በተለይ ዘንድሮ ሽመልስ በውድድር ዓመቱ ሳይጠናቀቅ ከወዲሁ ሰባት ጎል ማስቆጠር ችሏል ። 

ሽመልስ በቀለ ከዚህ በኋላ ሁለት ጎሎችን ማስቆጠር ሚችል ከሆነ የፔትሮጀት የምንግዜውም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ እንደሚሆን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል። “እስካሁን በፔትሮጄት አምስተኛ ዓመት ቆይታዬ በድምሩ 34 ጎል አለኝ።  ከዚህ በኋላ ባሉት ቀሪ ጨዋታዎች ሁለት ጎሎችን የማስቆጥር ከሆነ በ36 ጎል የፔትሮጀት የምንግዜውም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ እሆናለው። አሁን ለጊዜው ስሙን ያልያዝኩት ተጨዋች 35 ጎል በማስቆጠር የፔትሮጀት የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን እየመራ እንደሚገኝ አውቃለው ። ከፈጣሪ ጋር በቀጣይ ለቡድኔ የሚገባውን አገልግሎት እየሰጠው በግሌ ይህን ታሪክ ማሳካት እፈልጋለው።” ብሏል።