የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ቅድመ ውድድር ዝግጅት | ሲዳማ ቡና

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚሳተፉ ክለቦች ለዘንድሮው የውድድር ዘመን ያሳለፉትን የዝግጅት ጊዜ በሚያስዳስሰው ፅሁፋችን የዛሬ ተረኛው ሲዳማ ቡና ነው።

ከታችኛው የሊግ ዕርከን መጥተው በፕሪምየር ሊጉ የተሻለ ብቃት በማሳየት ይጠቀሱ ከነበሩ ጠንካራ ክለቦች መካከል ሲዳማ ቡና አንዱ ነው። ሆኖም ይህ ጥንካሬው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቶ ያለፉትን ሶስት የውድድር ዓመታት ያስመዘገበው ውጤት እየወረደ ሲሄድ ታይቷል። ለአብነትም አምና ያሳለፈውን የውድድር ዓመት ማስታወስ ይገባል። 2010ን በአሰልጣኝ ዓለማየሁ አባይነህ ስር የጀመረው ሲዳማ ከውድድሩ አጋማሽ በኋላ ከአሰልጣኙ ጋር መዝለቅ አልቻለም። ክለቡ በመጀመሪያው ዙር ያጋጠመውን የውጤት መንሸራተት ተከትሎ አመራሮቹ በሰጡት አፋጣኝ ውሳኔ አሰልጣኙን ከቦታቸው በማንሳት በወቅቱ ምክትል አሰልጣኝ የነበረው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት ሾመዋል። በቀጣይ ጊዜያትም ሲዳማ ከነበረበት የውጤት ቀውስ ወጥቶ እና በመጠኑ ከወራጅ ቀጠናው ርቆ በሊጉ መቆየት ችሏል። በ30 የሊግ ጨዋታዎች 9 አሸንፎ ፣ 11 አቻ ወጥቶ እና 10 ጊዜ ተሸንፎ በ38 ነጥቦች 8ኛ ደረጃን ይዞ ነበር ያጠናቀቀው። ክለቡ በአማካይ በጨዋታ አንድ ግብ ቢያስቆጥርም 33 ግቦችን በማስተናገዱ ዓመቱን በሶስት የግብ ዕዳ እንዲያጠናቅቅ ሆኗል።

በአዲሱ የውድድር ዓመት ሲዳማ ቡና በብዙ መልኩ ተቀይሮ ይመጣል። በይርጋለም ስታድየም ጨዋታዎቹን ያደርግ የነበረው ክለቡ መቀመጫውን ወደ ሀዋሳ በመቀየር ሀዋሳ ከተማ እና ደቡብ ፖሊስ ወደሚጠቀሙበት ሰው ሰራሽ ሜዳ ለመምጣት መወሰኑ ዋነኛው ለውጥ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ አሰልጣኝ ይቀጥራል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው ሲዳማ ከአሰልጣኝ ዘርአይ ሙሉ ጋር የአንድ ዓመት ውል መፈራረሙን እናገኛለን። በተጨማሪም ምክትል አሰልጣኝ የነበረው ካሳሁን ገብሬን በማሰናበት ሁለት ረዳት አሰልጣኞችን አምጥቷል። የቀድሞው የደቡብ ፖሊስ ፣ ስልጤ ወራቤ እና ኢትዮጵያ ውሀ ስራ አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ እና በነቀምት ከተማ ረዳት የነበረው ስንታየሁ ግድየለው ናቸው የአሰልጣኝ ዘርዓይ ምክትል በመሆን የተቀጠሩት። ከዚህ ውጪ ሲዳማ ውላቸውን ከጨረሱ እና አቋማቸው ወርዷል ካላቸው በርካታ ተጫዋቾቹ ጋር ተለያይቷል። ከነዚህ መካከልም አምበሉ ፍፁም ተፈሪን ጨምሮ ባዬ ገዛኸኝ ፣ አበበ ጥላሁን ፣ አብይ በየነ ፣ ወንድሜነህ ዘሪሁን ፣ አዲስአለም ደበበ ፣ አብዱለጢፍ መሀመድ ፣ መሀመድ ኮናቴ ፣ ማይክል አናን እና አሻዬ ኬኔዲ ይጠቀሳሉ።


ሲዳማ ለዘንድሮው የውድድር ዘመን ክፍተት አለብኝ ባላቸው ቦታዎች ላይ ያመነባቸውን አስር አዳዲስ ተጫዋቾች ከፕሪሚየር ሊግ እና ከፍተኛ ሊግ ክለቦች ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል። ግርማ በቀለ (ተከላካይ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ) ፣ ተስፉ ኤልያስ (ተከላካይ ከወላይታ ድቻ) ፣ ዳዊት ተፈራ (አማካይ ከጅማ አባቡና) ፣ ሚሊዮን ሰለሞን (ተከላካይ ከአዲስ አበባ ከተማ) ፣ ዳግም ንጉሴ (ተከላካይ ከአዲስ አበባ ከተማ) ፣ ሰንደይ ሙቱኩ (ተከላካይ ከፋሲል ከተማ) ፣ ገዛኸኝ በልጉዳ (አጥቂ ከነቀምት ከተማ) ፣ አበባየሁ ዮሀንስ (አማካይ ከደቡብ ፓሊስ) ፣ አዱኛ ፀጋዬ (ግብ ጠባቂ ከቆይታ በኃላ የተመለሰ) እና ተመስገን ገ/ፃዲቅ (አጥቂ ከመከላከያ) አዳዲሶቹ ፈራሚዎች ሲሆኑ ለወላይታ ድቻ እና አዳማ ከተማ በውሰት ተሰጥተው የነበሩት ፀጋዬ ባልቻ እና ጫላ ተሺታም ወደ ክለቡ ተመልሰዋል። ከዚህ በተጨማሪም ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ ቢኒያም ላንቃሞ ፣ ፀጋአብ ብርሀኑ ፣ ቦንኬ ቱሲሳ እና አማኑኤል ኪሩቤልን አሳድጓል። ሲዳማ አምና ወጣ ገባ አቋምን እያሳየ ለመዝለቁ አንዱ ምክንያት ከውጭ ካስፈረማቸው አራት ተጫዋቾች መካከል በተለይም መሀመድ ኮናቴ ፣ አሻዬ ኬኔዲ እና አብዱለጢፍ መሀመድ በተጠበቁት መጠን ክለቡን አለማገልገላቸው እንደሆነ ይታመናል። ዘንድሮም ምንም እንኳን ክለቡ በርካታ ተጫዋቾች ያመጣ ቢሆንም በአጥቂ ስፍራ ላይ ከፍተኛ ክፍተት በመኖሩ ለ8 የውጪ ተጫዋቾች የሙከራ ዕድል ሰጥቶ ማሳመን ባለመቻላቸው ሳይቀጥራቸው ቀርቷል። አሁን ደግሞ ጃስተስ አኔኔ የተባለ ኬኒያዊ አጥቂን በመሞከር ላይ ይገኛል።

ሲዳማ ቡና ከነሀሴ 21 ጀምሮ በቀን ሁለት ጊዜ ልምምድ በማድረግ ለዘንድሮው የ2011 የፕሪሚየር ሊግ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ጀምሯል። ከአምና በዞረው የኢትዮጵያ ዋንጫም ሀዋሳ ከተማን ጥሎ አልፎ መስከረም ወር ላይ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታውን በማድረግ ዓመቱን ቢጀምርም እስከ ፍፁም ቅጣት ምት በዘለቀው ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተረቶ ከውድድሩ ወጥቷል። በመቀጠል ከጥቅምት 4-10 ድረስ በተካሄደው እና ሶስት ክለቦችን ብቻ ባሳተፈው የደቡብ ካስቴል ዋንጫ ላይ አራት ነጥቦችን ሰብስቦ የውድድሩ አሸናፊ መሆን ችሏል። አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉም የዝግጅቱን ጊዜ እንዲህ ሲል ይገልፀዋል ” በቡድኑ ውስጥ አዳዲስ ተጫዋቾች ተቀላቅለዋል። ካሉት ነባር ተጫዋቾች ጋር አዋህደንም ቡድኑ ምን ይመስላል የሚለውን ነገር በኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ ላይ ተመልከተናል። ከዚያም በኃላ ብዙ የወዳጅነት ጨዋታዎችን አድርገናል። ቡድኑን በተለያየ መልኩ እየከፈልን ለማየትም ችለናል። የተሻለ እና ጥሩ ቡድን እንደሆነም ተረድተናል። በመቀጠልም የሲቲ ካፕ ውድድር ነበር። ምንም እንኳን በውድድሩ ላይ ሶስት ቡድኖች ቢሳተፉም ጥሩ ጥሩ ፍሬ የታየበት ፤ መተዋወቅም ስላለ ጠንካራ ፉክክር የተደረገበት ነበር። በውድድሩም ሻምፒዮን ሆነናል። ይህ ደግሞ ሊጉ ሲጀምር ከፋሲል ጋር ላለብን ጨዋታ ለኛም ሆነ ለደጋፊው ጥሩ ስንቅ ነው የሚሆነን። ”

ክለቡ አምና ከፍፁም ተፈሪ እና ዮሴፍ ዮሀንስ በሚነሱ ኳሶች አጥቅቶ ለመጫወት ቢያስብም ፊት ላይ አጥቂው ባዬ ገዛኸኝ ውጪ ሌላ ተመራጭ ተጫዋቾች ባለመኖሩ እንዲሁም ባዬም በቀደመው አቋሙ ላይ ባለመገኘቱ በመስመር አጥቂው አዲስ ግደይ ላይ ጥገኛ ለመሆን ተገዷል። በመስመር ላይ ያደላው የቡድኑ አጨዋወትም ለተጋማችነት ሲያጋልጠው ተስተውሏል። ይህ ችግሩ ዘንድሮ እንደማይደገም በቦታው የነበረውን ጥንካሬ መመለስ ይጠበቅበታል ። እስካሁን በአመዛኙን በዝውውር ሂደቱ ላይ በተከላካይ እና በአማካይ ስፍራ ላይ ትኩረት ያደረገው ክለቡ ወሳኝ አጥቂ በጊዜ አለማምጣቱ እንደ ክፍተት የሚቆጠር መሆኑን ” እንደ ቡድን ቡድናችን ጥሩ ነው ፤ ግን ክፍተት የለብንም ማለት አይቻልም። በፊት መስመሩ ላይ ክፍተት አለብን አግቢ የሚባል አጥቂም ያስፈልገናል።” የሚለው የአሰልጣኙ አስተያየት ማረጋገጫ ነው።

አምና በመሀል ኃላፊነት የተረከበው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ምንም እንኳን በሊጉ ረዘም የአሰልጣኝነት ቆይታ ባይኖረውም በጊዜው የነበሩትን ችግሮች በመቋቋም ነገሮችን ለማስተካከል እንደሞከረ ይናገራል። ሆኖም በቢጫ ካርድ ምክንያት እንዳጣቸው ሦስት ነጥቦች ያሉ ነገሮች እንቅፋት እንደሆኑበትም አልሸሸገም። በሁለተኛው ዙር ከነበረው አጭር ጊዜም አኳያ በቀድሞው አሰልጣኝ ዓለማየሁ አባይነህ ታክቲክ በመቀጠል ቡድኑን ማቆየት እንደቻለ የሚያምነው አሰልጣኙ ዘንድሮ ሊያሳየን ስላሰበው ሲዳማ ቡና ሲናገር ” ዘንድሮ ዘግይተን ወደ ዝውውር በመግባታችን ከመጀመሪያው ጀምሮ የፈለኳቸውን ተጫዋቾች ባላገኝም ጥሩ ወጣቶችን እንዲሁም በከፍተኛ ሊግ እና ፕሪምየር ሊግም የሚጫወቱ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን መሀል መሀል ላይ ቀላቅለን ከነባሮቹ ጋር በማድረግ ቡድናችንን በአዲስ መልክ አዋቅረናል። ዘንድሮ የተሻለ ነገርም ይኖራል ብለን እናስባለን። ምክንያቱም በዝግጅታችን ወቅት ወደ ስድስት ጨዋታዎችን አድርገናል ፤ ጥሩ ውጤትም አስመዝግበናል። ከስድስቱ አምስቱን አሸንፈናል። በነዚህ ጊዜያት ‘ቡድኑ ምን ይመስላል ? የምንፈልገውን አጨዋወትስ መተግበር ይችላል ወይ ?’ የሚለውን ነገር እያየን ነው። ተስፋ ሰጪ ነገርም እንዳለው መናገር ይቻላል። በመሆኑም ግሩም ኳስ የሚጫወት ቡድን ሰርተን የክለቡ ሪከርድ የሆነውን አራተኛ ደረጃን ለማሻሻል እና ደጋፊን የሚያስደስት እንቅስቃሴ ለማድረግ እንሰራለን።” ይላል።

በመጨረሻም አሰልጣኙ ባስተላለፈው መልዕክት “ለአንድ ቡድን መሠረቱ ደጋፊ ነው፡፡ የሲዳማ ቡና ደጋፊዎችም ትልቅ አቅም ያላቸው ናቸው። ዘንድሮም ክለቡ የነሱን ድጋፍ ስለሚፈልግ ከጎኑ በሚገባ ሊቆሙ ይገባል። ይህን እንደሚያደርጉም ትልቅ እምነት አለኝ። እነሱ እንደ አስራ ሁለተኛ ተጫዋች ሆነው ያግዛሉ የሚል እምነት አለኝ። ለነሱም ያለኝ አክብሮት እጅግ ታላቅ ነው። ” በማለት ሀሳቡን ያጠቃልላል።

ሲዳማ ቡና የፊታችን ጥቅምት 17 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሲጀመር በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ የአሰልጣኝ ውበቱ አባተን ፋሲል ከነማን በማስተናገድ ይጀምራል፡፡