የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ቅድመ ውድድር ዝግጅት | ድሬዳዋ ከተማ

በሳምንቱ መጨረሻ በሚጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ቡድኖች የዝግጅት ጊዜ ዙሪያ የሚያጠነጥነው ፅሁፋችን በመቀጠል ወደ ብርቱካናማዎቹ ይወስደናል።

የበርካታ ተጫዋቾች መፍለቂያ እንደሆነች የሚነገርላት ድሬዳዋ በፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ የሆነው ክለቧ በ2004 ከወረደ በኋላ ዳግም ወድ ሊጉ የተመለሰው በ2008 ነበር። ነገር ግን በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ክለቡ በሚፈለገው ደረጃ ላይ ለመገኘት ተቸግሮ ቆይቷል። በ2010 የውድድር ዓመትም እንደ ቀደመው ጊዜ ሁሉ እስከ 30ኛው ሳምንት ድረስ በመውረድ ስጋት ውስጥ ቆይቶ በግብ ልዩነቶች ከተረፉ አራት ቡድኖች መካከል አንዱ በመሆን የውድድር ዓመቱን ዘግቷል። ድሬዎች አምና በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ስር ሆነው ከበርካታ ዝውውሮች ጋር ዓመቱን ቢጀምሩም ከሰባተኛው ሳምንት በኋላ ከአሰልጣኙ ጋር አብረው መዝለቅ አልቻሉም። በተቀሩት 23 ሳምንታት ከአሰልጣኝ ስምዖን አባይ ጋር በመሆን የውድድር ዓመቱን የጨረሱት ብርቱካናማዎቹ በመጨረሻዎቹ ሳምንታት የሰበሰቧቸው ነጥቦች ነበሩ በሊጉ እንዲቆዩ ያደረጓቸው። በውጤት በኩል 14 ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት ፈፅመው ሰባት ጊዜ ሲያሸንፉ በዘጠኝ ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግደዋል። እጅግ ደካማ በሆነ ንፃሬም (በአማካይ በጨዋታ 0.46) 14 ግቦችን ብቻ ማስቆጠር ሲችሉ በተቃራኒው ከጨረሱበት ደረጃ አንፃር ሲታይ በሚያስገርም መልኩ የሊጉ ሁለተኛ ዝቅተኛ ጎል ያስተናገደ ክለብ (14) መሆን ችለዋል።

በክረምቱ ወራት ክለቡ ደረጃውን ለማሳደግ በማሰብ ከወሰዳቸው እርምጃዎች የመጀመሪያው የአሰልጣኝ ቅጥር መፈፀም ነበር። ክለቡ አዲስ አዳጊው መቐለ ከተማን በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ አድርገው በአራተኛነት ለመጨረስ ያበቁት አሰልጣኝ ዮሃስ ሳህሌን ነበር ምርጫው ያደረገው። አሰልጣኝ ስምዖን አባይ እና አሰልጣኝ ፍሰሃ ጥዑመልሳን ደግሞ ከመውረድ የታደጉትን ክለብ በምክትል አሰልጣኝነት በማገልገል ቀጥለዋል። በሌላ በኩል ድሬዳዋ ከነበሩት ተጫዋቾች መካከል ከግማሽ በላይ ከሚሆኑት ጋር ተለያይቷል። አህመድ ረሺድ ፣ ዮሴፍ ዳሙዬ ፣ ሱራፌል ዳንኤል ፣ ጀማል ጣሰው ፣ ያሬድ ዘውድነህ ፣ አናጋው ባደግ ፣ ዮሴፍ ድንገቶ ፣ በረከት ይስሀቅ ፣ያሬድ ታደሰ ፣ ዘሪሁን አንሼቦ ፣ ሙህዲን ሙሳ ፣ ኢማኑኤል ላሪያ ፣ ኩዋሜ አትራም ፣ ሳውሬል ኦልሪሽ እና ሚካኤል አኩፎ በዚህ ዝርዝር ውስጥ የሚካተቱ ናቸው። ዘንድሮ በድሬዳዋ መልያ የማንመለከታቸው ተጫዋቾች መበራከትም እንደሌሎቹ ክለቦች ሁሉ ድሬንም በየዓመቱ አዳዲስ ቡድን የመገንባት አዙሪት ውስጥ ከቶታል።  ከአሰልጣኝ ቡድን አባላት እና ተጫዋቾች ለውስጥ በተጨማሪ በድሬዳዋ ዘንድሮ የሚኖረው ለውጥ የስታድየም ነው። ከ1968ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ጀምሮ በአገልግሎት ላይ የሚገኘው የከተማዋ ስታድየም ዕድሳት ላይ የሚገኝ በመሆኑ ክለቡ የመጀመሪያዎቹን ጨዋታዎች የሚያደርገው በሁለተኝነት ወዳስመዘገበው የሐረር ስታድየም በመሄድ ይሆናል።

በጣም ጥቂት የሚባሉ ተጫዋቾቹን ብቻ ያቆየው ድሬዳዋ ክረምቱን ተጧጡፎ በሰነበተው ገበያ በለቀቁት ምትክ 16 ዝውውሮችን አጠናቋል። አዳዲሶቹ ፈራሚዎች ፍቃዱ ደነቀ (ተከላካይ ከመቐለ ከተማ) ፣ ሚኪያስ ግርማ (ተከላካይ ከባህርዳር ከተማ) ፣ ገናናው ረጋሳ (ተከላካይ ከአዲስ አበባ ከተማ) ፣ ሳሙኤል ዮሃንስ (አማካይ ከአውስኮድ) ፣ ኃይሌ እሸቱ (አጥቂ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ) ፣ ራምኬል ሎክ (አጥቂ ከፋሲል ከነማ) ፣ ምንተስኖት የግሌ (ግብ ጠባቂ ከደደቢት) ፣ ፍሬዘር ዘሪሁን (ግብ ጠባቂ ከአዲስ አበባ ከተማ) ፣ ዮናታን ከበደ (አጥቂ ከወላይታ ድቻ) ፣ ምንያህል ይመር (አማካይ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ) ፣ አማረ በቀለ(ተከላይ ከወልዲያ) ፣ ቢኒያም ፆመልሳን (ከናሽናል ሲሚንት) ፣ ኢታሙና ኬይሙኒ (አማካይ ከቱራ ማጂክ ናሚቢያ) ፣ ሰይላ አብዱላሂ (አጥቂ ከጊኒ)፣ ኢዝኬል ቲቴ (አጥቂ ከጋና) እና ፍሬድ ሙሺንዲ (አማካይ ከኮንጎ ዲ.ሪ) ሲሆኑ በድሬዳዋ ከ20 ዓመት በታች ቡድን ጋር እየሰሩ የሚገኙት ዳዊት ባዩ ፣ እዮብ ታ፣ ሰይፉ ታከለ እና አላዩ ተቀባ ወደ ዋናው ቡድን አድገዋል።

©Dire Kenema official

“ዘግይቼ ቡድኑን በመረከቤ ልንመለምላቸው ያሰብናቸው ተጫዋቾች እንዲያመልጡን ሆኗል።  ከአሜሪካ ፣ ፈረንሳይ ፣ አውስትራሊያ እና ጀርመን ለመጡ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ፣ ከድሬዳዋ ለተገኙ 19 ወጣቶች እንዲሁም ዘጠኝ የውጪ ዜጎች ጨምሮ 38 ለሚሆኑ ተጫዋቾች የሙከራ ዕድል ሰጥተናል። በመሆኑም በምልመላው ፈታኝ የሆነ የቅድመ ውድድር ዝግጅት ጊዜ ነበር ያሳለፍነው። በተቻለን መጠንም ከፕሪምየር ሊጉ እና ከፍተኛ ሊጉ የተሻሉ ያልናቸውን ተጫዋቾች አካተናል። ከዚህ ባለፈም ዛሬ የመጨረሻ የኢንተርናሽናል ዝውውር ቀን በመሆኑ ስንመለከታቸው ከቆዩት ተጫዋቾች መካከል የምናስፈርማቸውን ይኖራሉ። ” ይላሉ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ስለዝውውር ጊዜው ያላቸውን አስተያየየት ሲሰጡ። በርግጥም ቡድኑ ጠንካራ ከነበረው የተከላካይ ክፍሉ ውስጥ እንደ በረከት ሳሙኤል እና አንተነህ ተስፋዬ የመሳሰሉ ተጫዋቾችን ማስቀረቱ እንደሚጠቅመው ቢታሰብም በሌሎቹ የቡድኑ ክፍሎች ላይ በተለይም በፊት መስመሩ ላይ አሰልጣኙ ከፍተኛ ስራ እንደሚጠብቃቸው ይታመናል።

ድሬዳዋዎች መስከረም 27 ነበር በባህርዳር ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን የጀመሩት። ከአንድ ሳምንት ቆይታ በኋላም በትግራይ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ወደ መቐለ አምርተዋል። በውድድሩም እስከፍፃሜው ድረስ መዝለቅ ይቻሉ ሲሆን  ፍቃዱ ደነቀ እና ራምኬል ሎክን በምርጥ ተከላካይ እና አጥቂነት ማስመረጥ ችለዋል። ከትግራይ ዋንጫ መጠናቀቅ በኋላ የተወሰኑ ቀናትን እዛው ካሳለፉ በኋላ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ልምምዳቸውን መስራት ቀጥለዋል። የትግራይ ዋንጫ ላይ መሳተፋቸው የአዳዲሶቹን ተጫዋቾች የተናጠል ብቃት ለመመዘን  እንደረዳቸው የሚያምኑት አሰልጣኝ ዮሃንስ የዝውውሮቹ መበራከት የዝግጅት ጊዜያቸውን እንዳከበደው ያስባሉ። ” ቡድኑ ብዙ ተጫዋቾች ወጥተውበታል። ከግብ ጠባቂ ጀምሮ ፣ ተከላካይ መስመር ላይ ፣ በተከላካይ አማካይ ቦታ ላይ ፣ በክንፍ እና በአጥቂ ቦታ ላይም ብዙዎቹ ለቀውብናል። በመሆኑም ሙሉ ቡድን መገንባት ይጠበቅብን ነበር። ስለዚህ የተፈጠሩትን ክፍተቶች በአግባቡ መሙላት የቅድመ ውድድር ዝግጅቱ ዋነኛው ስራችን ነበር። ” ከሚለው አስተያየታቸውም መረዳት የሚቻለው ይህንኑ ነው።

ድሬዳዋ ከተማ ወደ ከፍተኛ ሊጉ እንዳይወርድ ያደረገው ጥቂት ግብ ብቻ ያስተናገደው የኋላ መስመር ጥንካሬው እንደሆነ መናገር ይቻላል። የወጡ ተጫዋቾች ቁጥር ከፍተኛነት ግን በዚህ ጠንካራ ጎኑ ላይ ተመስርቶ ቡድኑን በማሻሻል እንዲሁም ደካማ ጎኖቹን በማስተካከል የመምጣቱን ሂደት ከባድ ያደርገዋል። አምና በነበሩበት መቐለ ከተማ በተመሳሳይ በቀላሉ ግብ የማያስተናግድ ቡድን ለገነቡት አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌም የአምናው የድሬ ጥንካሬ ጥሩ ግብዓት መሆን በቻለ ነበር። የቡድኑ በአዲስ መልክ መዋቀር ግን አሰልጣኙ  አዲስ ገፅታ ያለው ድሬዳዋ ከተማን ይዘው እንደሚመጡ በሚገባ የሚጠቁም ነው። ያም ቢሆን የቀድሞው የመቐለ ፣ ደደቢት እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የውድድር ዓመቱ አላማቸው ወጥነት ያለው የቡድኑ መገለጫ የሆነ አጨዋወትን ማምጣት ላይ ሳይሆን እንደሁኔታው እና እንደተጋጣሚዎች የተለያየ መልክ የሚይዝ ውጤት ተኮር ቡድን መገንባት ላይ ይመስላል ፤ የመጨረሻው አስተያየታቸውም ይህን የሚጠቁም ነው። ” ዋናው አላማችን ከአምናው የተሻለ ደረጃ ላይ የሚደርስ ቡድን መገንባት ነው። የመጀመሪያው ትኩረታችን ይህ ነው። የትኛውንም ዘዴ ብንጠቀምም መንገዶቹ ውጤት የሚያመጡ መሆናቸው ላይ እናተኩራለን። ከዚያ በተረፈ ግን ወጥ የሆነ አንድ አይነት አጨዋወት አንጫወትም ፤ ምክንያቱም የሚገጥሙን ቡድኖች ሁሉ አንድ አይደሉም። የተጋጣሚዎቻችን ደካማ እና ጠንካራ ጎኖች ላይ ተመስርተን ለማሸነፍ እንጫወታለን እንጂ በተመሳሳይ አቀራረብ ተገማች ለመሆን አናስብም። ቡድኑ ከግማሽ በላይ አዲስ ስብስብ ይዞ የሚሰራ በመሆኑም በአንድ ጊዜ የቡድኑ መገለጫ የሆነ አጨዋወትን ለማምጣት ከባድ ነው። ያን ለማድረግ አራት ወይም አምስት ዓመታትን ማሰልጠን ፣ በተመሳሳይ የቡድን መዋቅር መዝለቅ እና የሚፈለጉ ተጫዋቾችን ማግኘት ይጠይቃል። ስለዚህም የኛ ዋና አላማ ውጤታችንን ጥሩ ሊያደርግልን የሚችል ማንኛውንም ዘዴ ተጠቅመን ከተጋጣሚዎቻችን ተገቢውን ውጤት መሰብሰብ ነው። ”

በዚህ ሳምንት ማብቂያ በሚጀምረው ውድድር ድሬዳዋ ከተማ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2011 የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሜዳው ውጪ አዲስ አባባ ላይ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያደርጋል።