የፕሪምየር ሊግ ክለቦች የቅድመ ውድድር ዝግጅት | ሀዋሳ ከተማ 

የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ለዘንድሮው የውድድር ዘመን በምን መልኩ እየተዘጋጁ እንደሆነ በተከታታይ እያስዳሰስናችሁ በምንገኝበት መሰናዶ ሀዋሳ ከተማን እንዲህ ተመልክተነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአዲስ አካሄድ ሲጀመር ከነበሩ ስምንት ክለቦች አንዱ የነበረው ሀዋሳ ከተማ እስካሁን ሳይወርድ በመቆየት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ብቸኛው ክለብ ነው። አምና ጅማ አባ ጅፋር ዋንጫውን እስካነሳበት ጊዜ ድረስም የሁለት ጊዜ ሊጉ ቻምፒዮን ሀዋሳ ከተማ ከአዲስ አበባ ውጪ የሚገኝ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ያነሳ ክለብ ሆኖ ቆይቷል። ይሁንና ከአምስት ዓመታት ወዲህ በቋሚነት ላለመውረድ ከሚታገሉና ከወገብ በታች ሆነው ከሚያጠናቅቁ ክለቦች ተርታ ተሰልፏል። በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እየተመራ ለተመልካች ሳቢ የሆነ አጨዋወትን ቢከተልም ከሜዳው ውጭ ድል ካስመዘገበ ከአንድ ዓመት በላይ አስቆጥሯል። በሜዳው በአንፃራዊነት የተሻለ ነጥብ የሰበሰበው ሀዋሳ በመከላከያ በሰፊ የግብ ልዩነቶች ከመሸነፉ ውጭ አብዛኛዎቹን የሜዳ ላይ ጨዋታን አሸንፏል። በአጠቃላይ ከ30 ጨዋታ 8 አሸንፎ፣ 12 አቻ ወጥቶ፣ በ10 ደግሞ ሽንፈትን በማስተናገድ 27 ግብ አስቆጥሮ 36 ግቦችን ደግሞ አስተናግዶ 6 የግብ ዕዳን በመያዝ በ9ኛ ደረጃ ላይ አጠናቋል።

ሶስት ዓመታት ከግማሽ ክለቡን ከመሩት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር በዓመቱ መገባደጃ ከተለያየ በኃላ ምክትል አሰልጣኝ የነበረው ሙሉጌታ ምህረትን በዋና አሰልጣኝነት እንደሚቀጥር በስፋት ቢነገርም የቀድሞ የቡድኑ አምበል የብሔራዊ ቡድን ስራን በመያዙ ከ1990 ጀምሮ በምክትልነት እና በጊዜያዊ አሰልጣኝነት ሲሰሩ የነበሩትና በወልቂጤ ከተማ ሁለት ዓመታትን ቆይታ ያደረጉት አዲሴ ካሳን በዋና አሰልጣኝነት በሙሉጌታ ምህረት ቦታ ላይ ደግሞ በክለቡ በታዳጊ ቡድኑ ስኬታማ የነበረውና የኢትዮጵያን ከ17 ዓመት ብሔራዊ ቡድን በዋና አሰልጣኝነት የመራው ተመስገን ዳናን ረዳት በማድረግ ሾሟል። ከሊጉ ክለቦች ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ ዘግይቶ ወደ ዝውውር ገበያው የገባ ሲሆን በዘንድሮው ክረምት ጥቂት ተጫዋቾችን ያስፈረመ ክለብ ሆኖ ተመዝግቧል። እስከ አሁን አራት ተጫዋቾችን ብቻ ወደ ክለቡ የቀላቀለው ሀዋሳ ከተማ ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን በተከላካይ እና በአጥቂ ስፍራ ላይ ለማምጣት ጥረት ላይ መሆኑ ተሰምቷል። ክለቡን እስከ አሁን የተቀላቀሉት አዳነ ግርማ (አጥቂ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ11 ዓመታት በኋላ ክለቡን የተቀላቀለ)፣ ምንተስኖት አበራ (አማካይ አርባምንጭ)፣ ብሩክ በየነ (አጥቂ ከወልቂጤ ከተማ)፣ ያኦ ኦሊቨር (ተከላካይ ከአፍሪካ ስፖርትስ ) ሲሆኑ ለወራቤ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ በውሰት ተሰጥተው የነበሩት ገብረመስቀል ደባለ (አጥቂ) እና አክሊሉ ተፈራ (ተከላካይ) ዳግም ወደ ክለቡ ቀላቅሏል። 

ሀዋሳ ከተማ ካስፈረማቸው ተጫዋቾች ጋር ሲነፃፀር በርካታ ተጫዋቾችን ለቋል። ዳዊት ፍቃዱ፣ አብዱልከሪም ሀሰን፣ ፍሬው ሰለሞን፣ ጋብሬል አህመድ፣ መሐመድ ሲይላ፣ ሙሉዓለም ረጋሳ እና አላዛር ፋሲካ ከክለቡ ጋር የተለያዩ ተጫዋቾች ሲሆኑ ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ በውሰት ለዲላ ከተማ ሰጥቷል። ክለቡ በዘንድሮው የውድድር ዓመት እንደሁልጊዜው ሁሉ ከወጣት ቡድኑ በርካታ ተጫዋቾችን ያሳድጋል ተብሎ ቢጠበቅም ከ17 ዓመት በታች ግብ ጠባቂ የነበረው ምንተስኖት ጊንቦን ብቻ አሳድጓል። 

ክለቡ ካደረገው ጥቂት ዝውውር ባሻገር ከ2008 ጀምሮ ወደ ዋናው ቡድን ባደጉ 13 ወጣት ተጫዋቾች ላይ እምነቱን ጥሎ ከነሀሴ 25 ጀምሮ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በማከናወን ላይ ይገኛል። በደቡብ ካስቴል ዋንጫ እና በወዳጅነት ጨዋታዎች ራሱን ገምግሞ የሊጉን መጀመር በመጠባበቅ ላይ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ ዋና አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ የተጫዋች ስብስባቸውን የልምድ ስብጥር ለማመጣጠን እየሰሩ እንደሆነ ገልፀዋል። “በቅድመ ውድድር ዝግጅት ላይ የመጀመሪያ ስራችን የነበረው ያሉን ተጫዋቾችን በልምምድ እና በወዳጅነት ጨዋታዎች መገምገም ነበር። በክለቡ ውስጥ በየዓመቱ ከወጣት ቡድኑ ያደጉ ተጫዋቾች ቁጥራቸው እየጨመረ 13 ቢደርሱም እነዚህ ተጫዋቾች ግን በቂ ጨዋታ እየተጫወቱ አልነበረም። በወዳጅነት ጨዋታ ስንመለከታቸውም በፕሪምየር ሊግ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቆየት ስለሚያስቸግር አሁን ላይ ልምድ ባላቸው ተጫዋቾች የማመጣጠን እንቅስቃሴ ላይ ነን። በዚህም መሰረት የተከላካይ መስመር ተጫዋች ከውጪ ሀገር እየጨረስን ነው። የአጥቂ ተጫዋች ለማስፈረምም ተቃርበናል። የተከላካይ አማካይ ቦታ ላይ የቡድኑን ሚዛን የሚጠብቅ ተጫዋች አስፈርመናል። አዳነ ግርማም ትልቅ ልምድ አለው። በተረፈ ደግሞ እዚሁ ክለቡ ውስጥ ባለፉት ዓመታት ወደ ሌላ ክለብ ሄደው ራሳቸውን ፈትሸው የመጡ ሦስት ተጫዋች አሉን፤  እነዚህን አምጥተን ጥሩ ነገር ማሳየት እንችላለን ብለን እናምናለን። ” ብለዋል።

ባለፉት ተከታታይ የውድድር ዓመታት ከሚታወቅበት ተፎካካሪነቱ እየራቀ በመምጣት በደጋፊው ዘንድ ተቃውሞን ሲያስተናግድ የከረመው እና በተደጋጋሚ ባለመውረድ ስጋት ውስጥ ሆኖ የሚያጠናቅቀው ክለቡ ዘንድሮ ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰሩ አሰልጣኝ አዲሴ ይገልፃሉ። “ትልቁ ነገር ስራ ነው፤ መስራት ይፈልጋል። መስራት ማለት ሜዳ ላይ ከሚደረግ ስራ ባሻገር ከሜዳ ውጭ ላይ መሰራት ያለባቸው ነገሮች በሙሉ መሰራት መቻል አለባቸው። ደጋፊው አንዱ ኃይል ነው፤ ባለፈው ከሲዳማ ቡና ጋር ስንጫወት ያየነው ነገር ነው። ዙሪያውን በሲዳማ ቡና ደጋፊ ተከበን ነው የተጫወትነው። በዚህ ደጋፊ ውስጥ ሆኖ የተጫዋችን የስነልቦና ደረጃ አሳድጎ መቅረብ ከባድ ነው። ያም ሆኖ በደቡብ ካስቴል ዋንጫ ያሳዩት እንቅስቃሴ ለኔ ትልቅ ነገር ነው ይህም ውስጣችን የሆነ ጠንካራ ነገር እንዳለ ነው የሚያሳየኝ። የሀዋሳ ከተማ ችግር የባለቤትነት ስሜት ያለው ማጣቱ እንጂ ችግር ያለበት ቡድን ሆኖ አይደለም። በፊትም በክለቡ በነበርኩበት ወቅት ውጤታማ ስንሆን ትልቁ ነገራችን ኅብረታችን እና ውስጣችን የነበረው የባለቤትነት ስሜት ነው። አሁን ግን ይህ ያለ አይመስለኝም። ይህን ማስተካከል እና መስራት የምንችል ከሆነ አሁንም በፊት የነበረውን ሀዋሳ ከተማ ለመገንባት ምንም ችግር አይኖርብንም ብዬ አስባለሁ።” ሲሉ ይናገራሉ፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት ወደ ዋናው ቡድን ያደጉ 13 ተጫዋቾች

ባለፈው ዓመት ጥቂት ጎሎች ያስቆጠረው ሀዋሳ ከተማ ይህን አሻሽሎ ለመቅረብ በክረምቱ በውሰት ሰጥቶት የነበረው ገብረመስቀል ደባለ እና ብሩክ በየነን ከወልቂጤ ቢያመጣም በልምድ ያልዳበረ በመሆኑ ሊቸገር እንደሚችል ይገመታል። አሰልጣኝ አዲሴም ቡድኑ በፊት መስመሩ ላይ ክፍተት እንዳለበት ቢያምኑም ባሉት ተጫዋቾች ተጠቅመን ችግሩን እንቀርፋለን ይላሉ። “አምና የሀዋሳ ከተማን ዳታ ከተመለከትን በ30 ጨዋታ ያገባው 27 ግብ ነው፤ 33 ግብም ገብቶበታል። ይህን ስታይ የነበረብንን ድክመት ሁሉም የሚመለከተው ይመስለኛል። በደቡብ ካስቴል ዋንጫ ላይ ሶስት አስቆጥረን ሶስት ተቆጥሮብናል፤ አሁን ለተጠየቅኩት ጥያቄ ይሄ መልስ ሊሆን ይችላል። ቡድናችንን የለቀቁ ተጫዋቾች አብዛኛዎቹ ምንም ነገር ሳያደርጉ የለቀቁ አሉ። ከአራት ጎል በላይ ያስቆጠረም የለም። አሁን ይህን ጥያቄ ማንሳት ምንም አይጠቅምም። አሁን ጎል በማስቆጠር ላይ እንሻሻላለን የሚል ነገር አለን። አሁን የመጡት ታዳጊዎች ይህን የማድረግ አቅም ያላቸው ናቸው። “

በመጨረሻም አሰልጣኙ በጊዜ ሂደት ችግሮችን በማስተካከል ውጤታማ ቡድን ለመገንባት እየሰሩ እንደሆነ ገልፀው ከሜዳቸው ውጪ ውጤት የማጣት ችግር እና ላለመውረድ መጫወት ዘንድሮ ለመቅረፍ እንደሚጥሩ ተናግረዋል።  

ሀዋሳ ከተማ የፊታችን ዕሁድ በሜዳው ወልዋሎን ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲን በመግጠም የፕሪምየር ሊግ ጉዞውን ይጀምራል።